ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከከተማዋ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን በተለያዩ ሳይቶች በግንባታ ላይ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ሂደት በመጎብኘት ቤቶቹ በአፋጣኝ በሚያልቁባቸው ሁኔታዎች ላይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በጉብኝቱ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት በተለያዩ ስይቶች በግንባታ ላይ ያሉ የ40/60 እና 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ወሳኝ የሆኑ የሳይት ስራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ።ከሳይት ስራ በተጨማሪ የመንገድ ፣የመብራት ፣ የውሃ እና ፍሳሽ የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች በአብዛኛው ሳይቶች እየተሰራ ቢሆንም በአንዳንድ ሳይቶች ግን የውሃና ፍሳሽ ስራዎች ከግንባታው ጋር እኩል ባለመከናወናቸው የቤቶቹን ግንባታ እንዳዘገዩት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል ።የስራ ተቋራጮቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ እና ቤቶቹን አፋጣኝ ጨርሶ ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍም በሶስት ሺፍት 24 ሰዓት እንዲሰራም አቅጣጫ ተቀምጧል ።

በተጨማሪም ቤቶቹን በፍጥነት ለመጨረስ የሲሚንቶ እና መሰል የግንባታ ግብዓት አቅርቦት በአስቸኳይ እንዲቀርቡ ይደረጋል ብለዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው እንዲጠናቀቅ እንደ መንገድ፣ መብራት፣ ውሃ፣ ፍሳሽ እና ሌሎች የውጭ ምንዛሬን ለሚጠብቁ የመሰረተ ልማት ስራዎች መፍትሄ ለመስጠት በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን እና ለባለ እድሎችንም ይህንን ያገናዘበ የክፍያ እፎይታ ጊዜ እንዲራዘም የተደረገ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል ።