ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የዘንድሮውን የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ መርሐግብርን በማስመልከት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 60 የአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት ስራን በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።
በዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃግብር በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶችን ፣የፌደራል እና ልዩ ልዩ ተቋማት እንዲሁም ወጣቶችን በማስተባበር ከ2ሺህ በላይ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡
መርሐግብሩ በይፋ ከተጀመረ ጊዜ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ከ543 በላይ የአቅመ ደካማ ነዋሪ ቤቶች እድሳት እየተደረገ መሆኑን እና ከ130 በላይ ተጠናቀው ለነዋሪዎች ርክክብ መደረጉን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ስራ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ ስም ምክትል ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ነጻነት ዳባ በበኩላቸው በክፍለ ከተማው ዛሬው የተጀመሩትን 60 የአቅመ ደካሞች የቤቶችን ጨምሮ በጠቅላላው 190 የአቅመ ደካሞች የቤቶችን እድሳት ለማድረግ እቅድ መያዙን ገልጸው እስካሁን ከ130 በላይ ቤቶች እድሳት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡