14ኛው የስልጤ የባህል ፣የቋንቋና የታሪክ እንዲሁም የራስ አስተዳደር የተመሰረተበት 20ኛ አመት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፣የፌደራል እና የከተማችን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር ፣ የስልጤ ማህበረሰብ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት አደባባይ ተከብሯል ።አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች አንድነት ፣ ፍቅርና ህብረብሄራዊነት ማድመቂያ ናት ያሉት ወ/ሮ አዳነች የስልጤ ብሄረሰብ ከሌሎች እህት ወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን ከተማዋን እያለሙ ፤እያሳደጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በአብሮነት እና በአንድነት ከተሰራ በርካታ እድሎች እና ጸጋዎች አሉን ፤ ከተተባበርን እና ከተጋገዝን የኢትዮጵያን ብልጽግና ከማረጋገጥ ማንም የሚያስቆመን አካል እንደሌለ ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል ።ኢትዮጵያውንን እርስ በእርስ እንድንከፋፈል የሚያደርጉ አሉባልተኞችን ምንጫቸውን በማድረቅ እርስ በእርሳችን ተባብረን እና ተደጋግፈን ከሰራን የምንፈልገው እድገት እውን ማድረግ እንችላለን ሲሉ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አመልክተዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማም የስልጤን ማህበረሰብ የስራ ባህል እና ማንነት የሚያንፀባርቅ የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ በከተማ አስተዳደሩ እንደሚዘጋጅ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል ።