ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያን ወክሎ በኒጀር የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፈውን የቂርቆስ እጅ ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ሆቴል ተገኝተው ሸኝተዋል::
ክብርት ከንቲባ በሽኝቱ ወቅት እንደተናገሩት ማለፋቸውን ሲሰሙ እጅግ በጣም ደስ መሰኘታቸውን ገልፀው “እናንተ በመሳተፋችሁ ከውጤትም በላይ ባንዲራችን ከፍ ብሎ ይውለበለባል÷ መዝሙራችንም ለአፍሪካውያን ይደመጣልና ሀገራችንን በማስተዋወቅ ትልቁን አሻራችሁን በማስቀመጣችሁ ልትመሰገቡ ይገባል” ብለዋል።
በአንድ ክፍለ ከተማ ክለብ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ከፍ ስትል ከማየት በላይ ምንም አስደሳች ነገር የለም ያሉት ክብርት ከንቲባዋ እዚህ ያሳያችሁትን ብቃት እዛም በመድገም ውጤት አስመዝግባችሁ በድል እንደምትመለሱም እምነቱ አለኝና በርቱ ብለዋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚና የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ በበኩላቸው ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ክለቡ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ሲሰሙ የውድድሩን ሙሉ ወጭ በመሸፈናቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ቡድኑ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ያሸነፈ አሁንም የተጣለበትን ኢትዮጵያዊ አደራ በብቃት በመወጣት በውጤት እንደሚመለስ እምነቱ እንዳላቸው ገልፀዋል። በአስተዳደሩ ስምም መልካም ዕድል እንዲገጥማቸውም ተመኝተዋል።
በሽኝት መርሀ ግብር ላይ ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አብረሀም ታደሰና ሌሎች የከተማና የክፍለ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል
ቡድኑ ከዚህ በፊትም በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ካይሮ ላይ በመሳተፍ ውጤት ያስመዘገበ ቡድን መሆኑን ከወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያስረዳል::