በመስቀል የደመራ ሥነስርዓት እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የሽብር ተግባር በመፈጸም ሀገራዊ ቀውስ እንዲፈጠር በህቡዕ ሲያሴሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ አሸባሪ ቡድኖች በመስከረም ወር በሚከበሩት የአደባባይ በዓላት ላይ ሁከትና ብጥብጥ በመቀስቀስ ሀገራዊ ይዘት ወዳለው ቀውስ እንዲሸጋገር በህቡዕ ሴራ ሲጠነስሱ ነበር፡፡
ይሁንና የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የአደባባይ በዓላቱ ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ ባደረገው ጠንካራ ቅድመ ዝግጅትና ምስጢራዊ ክትትል ሴራውን ከውጥኑ ማክሸፍ ተችሏል፡፡ በዚህም 166 የህወሓት፣ የሸኔ፣ የአይ ኤስ እንዲሁም የኢመደበኛ አደረጃጀት አባለት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
የአሸባሪ ቡድኑ አባላት በመስቀል የደመራ ሥነስርዓት እንዲሁም የኢሬቻ በዓል በሚከበርባቸው አዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ ሁከትና ብጥብጥ የመቀስቀስ ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የጠቆመው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ፤ በተለይ አሸባሪው ሸኔ የሽብር ተግባር የሚፈጽሙ ሴሎችን ሲያደራጅ እና አባ ቶርቤ የተባለውን ገዳይ ቡድን ለማሰማራት ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሷል፡፡
ለዚሁ የጥፋት ተልዕኮውም ከህወሓት የሽብር ቡድን ጋር በመቀናጀትና የሎጀስቲክስ አቅርቦት በማመቻቸት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል፡፡
የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በሽብር ቡድኖች እና በተጠርጣሪ ግለሰቦች ህቡዕ እንቅስቃሴና የግንኙነት መረብ ላይ ሲያደርግ በነበረው ምስጢራዊ ክትትልም የአደባባይ በዓላቱን ወደ ቀውስ ለመቀየር ለታቀደው እኩይ ተልዕኮ መፈጸሚያ የሚሆኑ የቡድንና የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያዎች፣ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች፣ ቦምቦች እና በርካታ ጥይቶችን መያዙን ገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከአይ ኤስ የሽብር ቡድን ጋር በጋራ እንደሚሠሩና ከአሸባሪው ህወሓት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ እንደ ነበር የሚያስረዱ የሰነድ ማስረጃዎችም ተገኝተዋል ብሏል፡፡
መላው የጸጥታና ደኅንነት አካላት ተልዕኳቸውን በቁርጠኝነት ለመወጣት ቀን ከሌት መሥራታቸው እንዲሁም የኅብረተሰቡም የነቃ ተሳትፎ የታቀደው የሽብር ተግባር እንዲከሽፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ያመለከተው መግለጫው፤ በዘመን መለወጫ ወቅት የሚከበሩት የአደባባይ በዓላት የመላው ኢትዮጵያውያን የአብሮነት እሴት መገለጫና የጋራ ሀብት ናቸው፤ በርካታ ቱሪስቶችም የሚታደሙባቸው በመሆናቸው ተገቢው ጥበቃ ይደረግላቸው እንጂ የአንዳንድ የውጭና የውስጥ
ፀረ-ሰላም አካላት አጀንዳ ማስፈጸሚያ አይሆኑም ብሏል፡፡
በዓላቱ ሰላማዊ ድባብ የሰፈነባቸው እንዲሆኑ መላው ኅብረተሰብ ላሳየው ከፍተኛ ተሳትፎም ልባዊ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡