መመሪያውን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ እና የከተማዋ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ኮሚሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሚልኬሳ ጃጋማ እንደገለጹት መመሪያው አርሶ አደሩ የባለቤትነት መብቱ ተረጋግጦ በሕጋዊ ይዞታው ላይ በሚመቸውና በቻለው መልኩ ማልማት ያስችላል ብለዋል::መመሪያው በ5 ክፍለ ከተሞችና በ44 ወረዳወች ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን በቀጣይም ህገ ወጥ የመሬት ወረራን መከላከል የሚስችል የመሬት ምዝገባ ስርዓት እንደሚዘረጋም ዶክተር ሚልኬሳ ጃጋማ አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት ይሰሩ በነበሩ የከተማ ልማትና የማስፋፊያ ስራዎች ተገቢውን ካሳ እንደማያገኙ የገለጹ ሃላፊው የወጣው የይዞታ ማረጋገጫ መመሪያ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በዘላቂነት የሚፈታ እና የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡በራሳቸው ይዞታ ላይ የግብርና ስራ እያከናወኑ ያሉ አርሶ አደሮች ‘የግብርና መጠቀሚያ ሰርተፊኬት’ ይሰጣቸዋል ያሉት ሃላፊው አንድ አርሶ አደር ከአጠቃላይ ይዞታው ላይ በ500 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማከናወን እንዲችል በመመሪያው ተቀምጧል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የአርሶ አደር ልጆች በ150 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የመኖሪያ ቤት መገንባት እንዲችሉም እድል ይፈጥርላቸዋል በዚህም አርሶ አደሩ የባለቤትነት መብቱ ተረጋግጦ በሕጋዊ ይዞታው ላይ በሚመቻውና በቻለው መልኩ የማልማት እድል እንደሚፈጥር ዶ/ር ሚልኬሳ አብራርተዋል፡፡የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ በበኩላቸው የግብርና መጠቀሚያ ሰርተፍኬት አስፈላጊው ማጣሪያ ተደርጎ ለትክክለኛው ሰው ይሰጣል ብለዋል።ይህም አርሶ አደሩ ይወክለኛል ብሎ በየደረጃው በመረጠው ኮሚቴና በሌሎችም መንገዶች ማጣራት እንደሚደረግ በመመሪያው መካተቱን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ሂደቱ በከተማዋ የሚደረገው ልማት ሰው ተኮር እንዲሆንና ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ከልማቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።