በመርሐግብሩ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንዳስታወቁት አዲስ አበባ ከተማ የዲፕሎማቲክ እና የአለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ ምቹና ተመራጭ ሊያደርጋት የሚችሉ የጤና ማዕከላትን በመገንባት የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተጀምሯል ብለዋል ።የከተማ አስተዳደሩ ለኢጋድ የካንሰር ሕክምና ማዕከል መገንቢያ 20ሄክታር /200ሺህ ካሬ ሜትር መሬት/ከሊዝ ነጻ የሰጠ መሆኑን የገለፁት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ በሀገር ደረጃ ያዳበርነውን ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ የመፈፀም ልምድ ተግባራዊ በማድረግ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳስበዋል ።ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከተማ አስተዳደሩ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል ።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይ የካንሰር ህክምና እንዲስፋፋ ባለሙያዎችን ከማሰልጠን ባለፈ ግብዓት የሟሟላት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል ።ይህ የኢጋድ ቀጣናዊ የካንሰር ልህቀት ማዕከል ግንባታ መካሄድም ከሀገራችን አልፎ ለቀጠናው እና በአህጉሪቱ ጭምር ጥራት ያለው የካንሰር ህክምና ለመስጠት እና በዘርፉ ብቁ ባለሙያ ለመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል ።

ይህ ማዕከል በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጀምሮ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና ሌሎችም ለተጫወቱት ሚና ምስጋና አቅርበዋል ።

ማዕከሉ በቀጠናው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የካንሰር ጤና እንክብካቤ ችግርን ለመቋቋም እና የካንሰር በሽታን የመከላከል እና የማከም ችሎታ ያላቸው ብቁ ባለሙያዎችን ማሰልጠንን ያለመ መሆኑን የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ገልጸዋል ።ማዕከሉ ሲጠናቀቅም የካንሰር ምርመራን ፣ ህክምናን እና የተለያዩ ምርምሮችን ጨምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥራት ያላቸው የካንሰር እንክብካቤ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ዋና ጸሀፊው ጠቁመዋል ።ማዕከሉን ለመገንባት 500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሏል።

ማዕከሉ ሲጠናቀቅ የምርመራ ፣ ህክምና እና ጥናት እና ምርምርን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራት ያለው የካንሰር እንክብካቤ አገልግሎቶችን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡