ጉብኝቱ በዋናነት በእንጦጦና አንድነት ፓርክን ጨምሮ በወዳጅነት አደባባይና በቅርቡ ለዕይታ በበቃው የሳይንስ ሙዚየም የተካሄደ ሲሆን በጉብኝቱ 1200 የሚሆኑ የፈተና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኘው ገብሩ በጉብኝት መርሀ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት በከተማ አስተዳደሩ ፈተናው በተሰጠባቸው 9 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናው ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለተወጡ ፈታኞች ምስጋና አቅርበው ከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ቢሮ አማካይነት የሸገር ማስዋብ አካል የሆኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የፈተና አስፈጻሚዎች እንዲጎበኙ በማድረጉ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰማው አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ዲናኦል ጫላ በበኩላቸው ቢሮው የፈተና አስፈጻሚዎቹን በከተማው የሚገኙና የቱሪስት መዳረሻ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ከማስጎብኘቱ ባሻገር ፈተና አስፈጻሚዎቹ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ፈተናውን ያለምንም ችግር እንዲያስፈጽሙ የመኝታና የምግብ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው ፈተና አስፈጻሚዎቹም ከአቀባበል ጀምሮ በተደረገላቸው መስተንግዶ ለከተማ አስተዳደሩ እና ለትምህርት ቢሮ ምስጋና ማቅረባቸውን አስረድተዋል።