የአዲስ አበባ ከተማ የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቀነዓ ያደታ በከተማዋ ወቅታዊ ፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ መግለጫ ተሰጥተዋል።
የከተማዋን ሰላም የበለጠ ለማረጋገጥም በማንኛውም ግለሰብ እጅ የሚገኝ የጦር መሳሪያ ከዚህ ቀደም ያስመዘገበም ሆነ ያላስመዘገበ በአዲስ መልክ የማስመዝገብ እና የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት የተናገሩት ዶ/ር ቀነዓ በአካባቢው ወዳለ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ 2 ቀናት ማስመዝገብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በከተማዋ የሀሰት ወሬ ውዥንብሮች ቢኖሩም የአዲስ አበባ ፣ፌደራል ፖሊስ፣ የመከላከያ እና ከኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ካሉ ልዩ ዞን ሰላምና ደህንነት አባላት በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ዶ/ር ቀነዓ ጠቁመዋል።
የከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ጊዜያት በተለይ በህዝባዊ ፣ ሀይማኖታዊ እና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ካለምንም የፀጥታ መደፍረስ በሰላም እንዲካሄዱ እና ለከተማዋ አጠቃላይ የጸጥታ ስራ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው አሁንም ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ተናግረዋል::
መከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎችን በተመለከተ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ላይ የሚሳተፉ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድም ኃላፊው አስጠንቅቀዋል።
በቀጣይ ቀናትም የአዲስ አበባን ሰላም ለማስከበር የፍተሻ ስራዎች በተለያዩ ቤቶች እና የንግድ ቦታዎች ፍተሻ እንደሚደረግባቸው የገለጹት ሃላፊው ለዚህም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።