በአዲስ አበባ ከተማ ከ200 ሄክታር በላይ በሚሆኑ ቦታዎች የአረንጓዴ ልማት ስራዎች መሰራታቸውን የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማን አረንጓዴ ውበት የምንጠብቅበት ዘዴ በከተማዋ ደረጃ የተዘጋጀ የአረንጓዴ ቦታን በተቀመጠው ፕላን መሰረት በማልማት ነው ሲሉ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር እንደሻው ከተማ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ገልጸዋል።
የአረንጓዴ ውበት ልማቱ በ3 መንገድ ሊለማ ይችላል ያሉት አቶ እንደሻው፣ አንደኛው ውበት በሚባል የልማት ዓይነት፣ ሁለተኛው ጥላ ዛፍ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ እንደ ፍራፍሬ ያሉትን በመትከል ማልማት እንደሚቻል ነው ምክትል ኃላፊው ያብራሩት ።
በከተማዋ ብዛት ያላቸው የአረንጓዴ ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ልማት በማልማት ቀጣይነት እንዲኖራቸው እና ውበታቸውን በሚያስጠብቅ መልኩ የሚንከባከቡ ሶስት አካሎች አሉ ብለዋል።
1ኛው ህብረተሰቡ ራሱ የሚንከባከበው፣ 2ኛው በከተማ ደረጃ የስራ እድል ፈጠራ ተብለው የሚደራጁ የከተማ ወጣቶች ሲሆኑ፣ 3ኛው ደግሞ በራሱ ተቋሙ የሚንከባከብበት ሁኔታ እንዳለ ነው አቶ እንደሻው የተናገሩት።
የአረንጓዴ ሽፋናችን ማህበረሰቡ የራሱ መሆኑን አምኖ እና ኑሮውን የሚያሻሽል መሆኑን ተረድቶ በየደጁ በየቦታው ያለውን የአረንጓዴ ሽፋን በደንብ መያዝ እና መንከባከብ እንደሚገባ አቶ እንደሻው አሳስበዋል።