መምህራኑ እና የትምህርት ዘርፍ አመራሮች “የሚተካ ደም በመለገስ የማይተካውን ህይወት እናድን!”በሚል መሪ ቃል ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚሆን ደም ለገሱ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ከአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ጋር በመተባበር በተካሄደው የደም ልገሳ መርሃግብር የትምህርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ዘላለም ሙላቱ ፣የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ድንቅአለም ቶሎሳ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አበበ ፣መምህራን እና የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚሆን ደም ለግሰዋል፡፡
በደም ልገሳ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው ደም የለገሱት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ እንዳስታወቁት መምህራን የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን በእውቀትና በስነ- ምግባር ከማነጽ ባሻገር ሀገር የተለያዩ ፈተናዎች ሲገጥሟት ፈጥነው እንደሚደርሱ ገልጸዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊታችን የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር የህይወት መስእዋትነት ከመክፈል ጀምሮ የተለያዩ ችግሮችን ተቋቁሞ በግዳጅ ላይ ባለበት በአሁኑ ጊዜ መምህራን ደም ለመለገስና ደሞዛቸውን ለሰራዊታችን ድጋፍ ለማዋል በመወሰናቸው ከፍተኛ ምስጋና እንደሚገባቸው አቶ ሙላቱ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በትምህርት ሴክተሩ የሚከናወኑ መደበኛ ተግባራትን ከማከናውን ባለፈ ለህልውና ዘመቻው የሚደረገውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኃላፊው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ድንቅአለም ቶሎሳ በበኩላቸው በዛሬው የደም ልገሳ መርሀ ግብር የክፍለ ከተማ መምህራን ማህበር ስራ አስፈጻሚዎችን ጨምሮ ወደ 200 የሚሆኑ መምህራን ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመው የደም ልገሳ መርሀ ግብሩ በኢትዬጵያ ላይ ክህደት የፈጸሙ አካላትን በመመከት የህልውና ዘመቻውን በበላይነት ለሚመራው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚደረግ ድጋፍ መሆኑንና በቀጣይም በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ መምህራን በየትምህርት ቤቱ ተመሳሳይ የደም ልገሳ መርሀ ግብር እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል።