አዲስ አበባን የሽብር ቀጠና ለማድረግ የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን ዓላማ ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ 284 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
199 ሽጉጥ ከ2 ሺህ 453 ጥይት ጋር፣ 32 ክላሽንኮቭ ከ5 ሺህ ከሚልቅ ጥይት ጋር እንዲሁም 4 የጦር ሜዳ መነፅር ከተጠርጣሪዎቹ እጅ፣ ከስራ ቦታቸውና ከመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ለአሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረስ ተልዕኮ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ያከማቹት ከአንድ ኪሎ ተኩል በላይ የወርቅ እንዲሁም 37 ሺህ 294 ነጥብ 8 ግራም የብር ጌጣጌጥም መያዙን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪ ተጠርጣሪዎቹ ለሽብር ተግባር የሚጠቀሙባቸው የአዲስ አበባ ፣ፌዴራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ የማረሚያ ቤትና የራሱ የህወሓት የሽብር ቡድን አልባሳቶችም በቁጥጥር ስር መዋሉን እና በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ 123 የምርመራ መዝገብ መደራጀቱንም ምክትል ኮሚሽነሩ ገልፀዋል፡፡
የጥፋት ቡድኑ የትኛውንም ዓይነት ሽብር ከመፈፀም ስለማይቦዝን ህብረተሰቡ አካባቢውን ከመጠበቅ ባለፈ መረጃ በመስጠት ከፖሊስ ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
ኢቲቪ