በአዲስ አበባ ከተማ በኮቪድ-19 ቫይረስ በሽታ የሚያዙ ፣ በጽኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ቁጥር ከሌላው ጊዜ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ ህብረተሰቡ የኮቪድ-19 የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡
በትናንትናው ዕለት በኮቪድ-19 ቫይረስ በሽታ የሚያዙ ፣ በጽኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ቁጥር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን የ ኢንስቲቲዩት አስታውቋል።
በኮቪድ-19 ቫይረስ የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር ከ100 ቀናት በኋላ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል ያለው አንስቲቲዩት በትላንትናው ዕለት ለ7,518 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን 882 ግለሰቦች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።
ይህ ማለት ናሙና ከሰጡ 100 ግለሰቦች 12ቱ (12%) የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል ፤ይህ ደግሞ ከ100 ቀናት በኋላ በኮቪድ-19 የመያዝ ምጣኔ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
በአንድ ቀን ብቻ 22 ግለሰቦች ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የገቡ ሲሆን በአጠቃላይ 324 ግለሰቦች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ 10 ግለሰቦች በትላንትናው ዕለት በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል።
በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በዚህ ፍጥነት እጨመረ በመሄዱ ሕብረተሰቡ የኮቪድ-19 የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪውን አቅርቧል፡፡