የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በከተማዋ ከሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር የዋጋ ጭማሪና የኑሮ ውድነት ችግሮች ዙርያ ውይይት አድርገዋል ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በውይይት መድረኩ እንዳስታወቁት መንግስት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በከተማዋ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ህዝብና ሀገርን በማስቀደም በገበያ ላይ የምርት መስተጓጐል ሳይፈጥሩ ገበያ እንዲረጋጋ የበኩላቸውን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ጥራቱ አሳስበዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው ለውይይቱ መነሻ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት የሚመረቱ ምርቶች በደላላ በኩል እንዲያልፉ መደረጉ፤ምርቶችን ለተወሰኑ ቸርቻሪዎች ብቻ ማቅረብ፤የጅምላ ነጋዴዎች ሰንሰለት እንዲረዝም መደረጉ፤ከተመዘገቡ ምርት ማከማቻና መጋዘኖች ውጪ በተለያዩ ቦታዎች ምርትን ማከማቸት እና የመሳሰሉት ችግሮች በብዛት የሚስተዋሉ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከፌዴራል እስከ ከተማ የተዋቀረው የቁጥጥር ግብረሃይል የምርት አቅርቦትን በማያሻሽላሉ እና የንግድ ስርዓቱን በማያከብሩ አምራቾች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት አምራች ባለሃብቶች በበኩላቸው ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲፈታላቸው ጠይቀው ወደፊት በሙሉ አቅም በማምረት የኑሮ ውድነቱን ለማሻሻል ከመንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ የተናገሩ ተናግረዋል ።