ህገ-ወጥ የጦር መሳሪዎች እና ገንዘብ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ወንድይራድ ትምህርት ቤት አካባቢ ፖሊስ ሕብረተሰቡ የሰጠውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ባከናወነው ፍተሻ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የኮተቤ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሀላፊ ኮማንደር በየነ ዱሬሳ እንደገለፁት ህዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም ህብረተሰቡ የሰጠውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ፖሊስ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ለብርበራ በሄደበት ወቅት ግለሰቡ በፍተሻ እንዳይገኝበት በማሰብ 37 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር፣ 52 ሺሕ ብር እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን በፌስታል ጠቅልሎ ግቢው ውስጥ ደብቆ ተገኝቶበታል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የኮተቤ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የከተማችንን ሰላም ለማስጠበቅ እየተሰሩ እና የአሸባሪውን ህወሃት ሀገር የማፍረስ እንቅስቃሴ ለማክሸፍ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት ጋር በተያያዘ ከ2ሺህ በላይ የክላሽን-ኮቭ ጥይት፣ 2 ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ፣ 4 ሽጉጥ፣ 2 ጦር ሜዳ መነፅር፣ የእጅ መገናኛ ሬዲዮ ፣ ማህተሞችን እና ሲም ካርዶችን ህብረተሰቡ በሚሰጠው ጥቆማ እንዲሁም በብርበራ እና ፍተሻ መያዝ እንደቻለ የጣቢያው ሀላፊ ኮማንደር በየነ ዱሬሳ ገልፀዋል ።
ሀገርን ለማዳን የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ የፖሊስ አመራር እና አባላቱ ከሕዝብ ጋር በመተባበር ሌት ተቀን ያለ እረፍት ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ መስራት በመቻላቸው ጥሩ ውጤቶች ሊገኙ ችለዋል ብለዋል፡፡
ኮማንደሩ አያይዘውም ሕዝቡ በሀሰት መረጃ ሳይዘናጋና ሳይሸበር የአጥፊዎችን ሃገር የማፍረስ ዓላማ ተገንዝቦ በሀገሩ ላይ የተቃጣውን አደጋ በጠንካራ አንድነት ሊመክት እና ሰርጎ ገቦችን በመከታተል ለፖሊስ አስፈላጊውን መረጃ እና ጥቆማ እየሰጠ አካባቢውን በመጠበቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።