የከተማ አስተዳደሩ 100 ሺ ቤቶችን ለመገንባት ከጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ ኩባንያ ጋር የተደረሰው ስምምነት የትግበራ ሂደት ዙሪያ ምክክር እየተደረገ ይገኛል::
ኩባንያው በአዲስ አበባ በአራት ሳይቶች ለመገንባት በወሰደው ውል መሰረት እስካሁን የከወናቸውን ተግባራት ሪፖርት አቅርቦ ከአስገንቢው የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማት ቢሮ እንዲሁም ከአማካሪ መሃንዲሶችና ማህበራት ጋር ምክክር ተደርጓል ።
ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ በሳይቶቹ በቡልጋሪያ፣በላንቻ እንዲሁም በጣሊያን ኤምባሲ አቅራቢያ ወደ ግንባታ መግባት የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል::
የመሬት ባለይዞታዎች ጋር ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ሉያገኙት በሚችሉት ጥቅም እና መብት ላይ ሲሰራ ቆይቶ የአራቱም ሳይቶች ባለይዞታዎች በጥሬ ገንዘብ፣ በመኖሪያ ቤት (በከፊል የተጠናቀቀ) እንዲሁም ከምድር ቤት የጋራ ቦታ ላይ የሚያገኙት ድርሻ በዝርዝር ቀርቦላቸው በመስማማት ውሉን ፈርመዋል ተብሏል፡፡
ለባለ ይዞታዎች የሚሰጠው ገንዘብ እና መኖሪያ ቤት እንደቦታው ስፋት፣ የሚገነባው ሕንፃ ብዛት፣ በአንድ ወለል ላይ የሚኖረው መኖሪያ ቤት በሕንፃው ከፍታ ላይ የተመሠረተ ነውም ተብሏል::
ገንቢ/ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎችን በተመለከተ፤ በውል ስምምነቱ ውስጥ መብት እና ጥቅማቸው እንዲሁም ኃላፊነት እና ተግባራቸው በዝርዝር በውል ስምምነታቸው ቀርቦ ከተቀበሉት በኋላ ውሉን እንዲፈርሙ ተደርጓል ብሏል ኩባንያው፡፡
በዚሁ መሠረት 350ሺ ብር (200 ሺ ብር ለባለይዞታ 150ሺ ለገንቢው ጎጆ ብሪጅ) ከከፈሉ በኋላ በ4ቱም ሳይቶች ላይ ውሉን ፈርመዋል::
አምስት አማካሪ መሃንዲሶችን መርጦ ወደ ስራ የገባው ጎጆ ብሪጅ ሀውሲንግ አብዛኛውን ዝቅተኛ ገቢ የሕብረተሰብ ክፍሎች የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ ከ2ሺ ብር ጀምሮ በየወሩ በሪቮሌቪንግ ፈንድ በማስቀመጥ/ በመቆጠብ ከጎጆ ብሪጅ ሞዴል ጋር በማቀናጀት ይሰራልም ተብሏል::