ወንጀሉ የተፈፀመው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ጨው በረንዳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው።
የግል ተበዳይ አቶ ሳህሉ ሀኪም በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የንግድ ፍቃድ አውጥተው እንጀራ እያስጋገሩ የሚያከፋፍሉ ግለሰብ ናቸው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመምጣት ቆጣሪ ልናነብና ልንመረምር ነው ካሉ በኋላ የኤሌክትሪክ ቆጣሪውን አይተው 33 ሺህ ብር እንደቆጠረ ለግል ተበዳይ ይነግሯቸዋል፡፡ የግል ተበዳይ አቶ ሳህሉ ሀኪም ያልተጠቀሙበትን ፍጆታ እንደቆጠረባቸውና ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ሲያሥረዷቸው ከተፈቀደልህ በላይ ሃይል ጨምረህ ተጠቅመሃል በማለት የሁለት ቆጣሪዎች ሃይል እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እሱባለው ጌትነት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ባለሙያዎቹ 15 ሺህ ብር እጅ መንሻ ጉቦ ከሰጧቸው እንደሚያስተካክሉላቸው ለግል ተበዳይ ነግረው ገንዘብ መጠየቃቸውን የጠቀሱት ምክትል ኢንስፔክተር እሱባለው ጌትነት የግል ተበዳይም ይህን ያህል ገንዘብ እንደሌላቸው እና 10 ሺህ ብር እንዲያደርጉላቸው ተደራድረው ከጠየቋቸው ገንዘብ ውስጥ 5 ሺህ ብር ሲቀበሉ ቀደም ብለው ጉዳዩን ለፖሊስ አሳውቀው ስለነበር ከነ ገንዘቡ እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
ህዝብ እና መንግስት የጣሉባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው ህብረተሰቡን የሚያማርሩ ግለሰቦችን ለህግ አጋልጦ በመስጠት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ሲሉ የግል ተበዳይ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።