በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በንግግር እና ውይይት መፈታቱ ተገልጿል።
ቤተክርስቲያኗ ያጋጠማትን ፈተና ለመፍታት የሃይማኖት አባቶቹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ምክክር አድርገዋል።
በውይይታቸውም አንድነትን የሚያፀና እና አገልግሎትን የሚያሰፋ መንገድ መከተል ተገቢ መሆኑን በማመን ከስምምነት መደረሱን የሃይማኖት አባቶች ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል።
ከቋንቋ ጋር በተገናኘ የሚነሡ ሐሳቦችን ለመመለስ ቤተክርስቲያን የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ እንድትቀጥል ከመግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን በበጀት እና በሰው ኃይል ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶታል።
በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ እምነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ማሰልጠኛ ኮሌጅ እና ዩኒቨርስቲዎች እንዲጠናከሩ እና ቤተ እምነትን ለትውልድ ለማሻገር መፈታት የሚገባቸውን ችግሮች በጥናት እና በአሠራር መፍታት እንደሚገባም መተማመን መፈጠሩ በመግለጫው ተጠቁሟል።