በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዳይሰፍን የሚሰሩ የግጭት ነጋዴዎችን በጋራ በመከላከል አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረቡ።
የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክብረ በዓል ላይ ለመታደም ሐዋሳ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ እየነፈሰ ያለው የሰላም አየር ያላስደሰታቸው ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ኃይሎች ጽንፈኛ ሚዲያዎችን እና የግጭት ነጋዴ አክቲቪስቶችን በማሰማራት የዜጎችን ህይወት ለመቅጠፍ እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እነዚህ አካላት በተቀናጀ መንገድ የጥፋት አጀንዳ በመስጠት ኢትዮጵያን በግጭት አዙሪት ውስጥ ለማቆየት እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም አንድነታችንን በማጠናከር ይህንን እኩይ አካሄድ በጋራ መከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም መንግስት ሙስና እና የተደራጀ ሌብነትን ለመከላከል የጀመረው ጠንካራ እንቅስቃሴ ያስደነገጣቸው አካላት የተለያየ አጀንዳዎችን በመፍጠር ግጭት ለመቀስቀስ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉ ዜጎች እንዳሉ ሁሉ አገር ዘርፈው ለመበተን የሚሰሩ ሌቦች መኖራቸውንም መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያውያን መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ የግጭት ማዕከል ለማድረግ ጥረቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ሰሞኑን በአዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በማያያዝ ግጭት ለመቀስቀስ የተሞከረው ጥረት የዚሁ አካል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
እነዚህ አካላት እርስ በርሱ የሚጣረስ አጀንዳ በመፍጠር ህዝብን ሊያጋጩ ጥረት ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ሙስናን ለመታገል የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል፤ ህዝቡም ለዚሁ ስራ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
የጸረ ሙስና ትግሉን የግጭት አጀንዳ በመፍጠር ማስቆም እንደማይቻልም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የከተማ አስተዳደሩ ሙስና እና የተደረጀ ሌብነትን በቁርጠኝነት እንደሚታገል ያረጋገጡት ከንቲባዋ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላም ከማስጠበቅ ባሻገር የጸረ-ሙስና ትግሉን ማገዝ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የትምህርት ማህበረሰብ አባላት በትምህርት ቤቶች አካባቢ ግጭት ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራትን በመከላከል ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡