የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ልዩ ስብሰባ እንዲጠራ ከፈረሙ 52 አገራት ውስጥ አንድም አፍሪካዊ አገር አለመኖሩ ታወቀ፡፡
ይህም ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለው እሳቤ እንዲሁም የ”በቃ” #Nomore ንቅናቄ ፍሬ እያፈራ የመሆኑ አንዱ ማሳያ መሆኑ እየተጠቀሰ ነው፡፡
አፍሪካዊያንን በዳግም ቅኝ ግዛትና ጭቆና ካልዘወርን የሚሉ አሜሪካ መር ጽንፈኛ አገራት አፍሪካ ከእጃቸው እንዳትወጣ የነፃነት ምልክታቸው የሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ያለ የሌለ በትራቸውን ማሳረፍን እንደ ስልት ወስደዋል፡፡
ከዚህ መገለጫ ውስጥም የተገኘው የሰብኣዊ መብት ጥምር ምርመራ ሪፖርት ጥቅምት 24 ለሕዝብ ይፋ በሆነበት እና መንግሥትም በሪፖርቱ የተመላከቱ ምክረ ሐሳቦችን ተቀብሎ ወደ ተጨባጭ ተግባር በገባበት ወቅት የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈፀም የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ እንዲጠራ ፊርማ አሰባስበው አስገብተዋል፡፡
ሆኖም ፊርማውን ከፈረሙት 17 የምክር ቤቱ አባላትና 35 ታዛቢ አገራት ውስጥ አንድም አፍሪካዊ አገር አለመኖሩን ከዋልታ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የተወሰኑ አባል አገራት ለፖለቲካዊ ዓላማ ሲሉ የመንግሥትን ጥረት በመናቅ ልዩ ስብሰባ እንዲደረግ መጠየቃቸው ግራ የሚያጋባና የሚያበሳጭ እንደሆነ አሳውቋል፡፡
ምክር ቤቱ ቀዳሚ ትኩረት መስጠት የነበረበት የሽብር ቡድኑ ሕወሓት በአፋርና አማራ ክልል በፈፀመው የሰብኣዊ መብት ጥሰትና ወንጀሎች ላይ ምርመራ እንዲደረግ ማስቻል ነበር ያለችው ኢትዮጵያ፤ መንግሥት የዓለም ዐቀፍ ሕጎችን ባከበረ መልኩ ለሰብኣዊ መብት መጠበቅ በትጋት መስራቱን እንደሚቀጥልም ማሳወቋን መዘገባችን ይታወሳል፡፡