አዲስ አበባ ነሐሴ 4 ቀን 2014 ዓ.ም፡ በአዲስ አበባ ከተማ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት ስልሳ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በቀን ከሁለት ሺ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ድጋፍ ለአንድ ወር አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎቹ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት በነፃ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የግሪን ትራንስፖርት ስራ አስኪያጅ አቶ በሀይሉ ውብሸት ገልፀዋል፡፡ ህብረተሰቡ ስለ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ያለው ግንዛቤ እያደገ መምጣቱንና በቀጣይ አሁን ካለው የስምሪት መስመር በተጨማሪ ሌሎች መስመሮችን በማከል አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ከ40 በላይ የቻርጂንግ ማዕከላት ቻርጅ የሚደረጉት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎቹ በአስተማማኝ ሁኔታ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎችን በስፋት ለማስተዋወቅና ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ለማስቻል የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከግሪን ቴክ ኢትዮጵያ በተጨማሪ ማራቶን ሞተርስና ኮረንንቲ ሞተርስ የተሰኙ ተቋማት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረገ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ ያለው የማይገመት ተለዋዋጭ ዋጋን ለመቋቋም በኤሌክትሪክ ሀይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል አስፈላጊ በመሆኑ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ዘርፉን ለማሳደግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት ብቸኛ መንገዳችን የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን መጠቀም በመሆኑ ከተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ጋር በመተባበር ዘርፉን በተለያዩ ማበረታቻዎች ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ለአንድ ወር አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ አሁንም ተጨማሪ የስምሪት መስመሮችን በማከል አገልግሎታቸውን እያሰፉ እንደሚቀጥሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡