ሶስቱ ግለሰቦች በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 አካባቢ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታር ላይ ዝርፊያ ሲፈፅሙ በአካባቢው ነዋሪዎች በተሠጠ ጥቆማ ተይዘዋል፡የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በላከው መረጃ በግለሰቦቹ ላይ ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል ብሏል፡፡
በዝርፊያው 2 ሺህ 250 ሜትር የመካከለኛ መስመር ማስተላለፊ መስመሮች፣ 42 የምሰሶ ስኒዎች እና አራት የእንጨት ምሶሶዎች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል ተብሏል፡፡

በዚህ ምክንያትም በኮዬ ፈጬ ያሉ ደንበኞችና በአካባቢው የሚገኙ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ታዎሮች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተቋርጦባቸዋል፡፡በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታሩ ላይ በደረሰው የስርቆት ወንጀል ተቋሙ ከ353 ሺህ 623 ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበትም አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በተዘረፈው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታር ምክንያት የተቋረጠውን አገልግሎት ወደነበረበት ለመመለስ የመልሶ ጥገና ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ህብረተሰቡም መሰል እኩይ ተግባራትን እንዲከላከል የሚያጠራጥር ሁኔታም ሲከሰት ለፀጥታ አካላት ማሳወቅ እንዲሁም ወደ በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል መደወል ወይም በአቅራቢያ በሚገኝ የተቋሙ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ጥቆማ ማድረግ እንደሚገባው ገልጿል፡፡