እየተካሄዱ ያሉ ኮንፈረንሶችን በተመለከተ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ መለሰ በመግለጫቸው በ1860 መሠረታዊ ፓርቲ እየተከናወኑ ያሉ ኮንፈረንሶች በዋናነት ከጉባኤ ዝግጅት ጋር የሚያያዙ ሲሆን የጉባኤ ተሳታፊዎችም የሚመርጡበት እንደሆነ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በቀጣይ ለሚኖረው የፓርቲ ጉባኤ የሚያስቀምጣቸውን መሠረታዊ አቅጣጫዎች ላይ ቅድመ ውይይት ያደርጋሉ።
የዚህ ኮንፈረንስ ፋይዳው በፓርቲያችን ውስጥ የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።
የብልፅግና ፓርቲ በቅርቡ በምርጫ ተሳትፎ ከህዝቡ ያገኘው ድምጽ ዕድል መሆኑን በመግለጽ ይህ ዕድል ሀገራዊ ሀላፊነት ለመወጣት የተገኘ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ሀገሪቱ ያለችበት ፈተናዎች ለማሻገር፤ ሀገሪቱን ወደ ፊት ለማራመድ፤ የያዝነው ራዕይ እውን የሚደረግበት አጋጣሚ አድርጎ ነው የሚወስደው። ስለዚህ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ፓርቲያችን እስካሁን ያደረገውን ዝግጅት በሚመለከትና በቀጣይ ደግሞ ከፊታችን ያሉ በርካታ ፈተናዎች ለመሻገር የሚያስችል የውስጥ ጥንካሬ እና ብቃቱን የሚያረጋግጥበት መሆኑንም አንስተዋል።
ይህ ጉባኤ የፓርቲውን አላማ ለማሳካት የሚያስችል የፓርቲ ቁመና ለማጠናከር፤ ፓርቲው በህዝብ የተመረጠ ስለሆነ ከህዝብ የሚጠበቀውን ሀላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ቁመና እንዲይዝ የማድረግ ሀላፊነት ያለው ጉባኤ እንደሆነም ገልጸዋል።
ፓርቲው አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ደረጃ በሚመለከት ያጋጠሙ እና እያጋጠሙ ያሉ በርካታ ፈተናዎች መሻገር የሚያስችል የአመራር ብቃት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ጉዳዮችን በተመለከተ በጥልቀት በማየት ከለውጡ ጋር ተያይዞ እና ብልጽግና ፓርቲ እውን ከሆነ በኋላ እንደዚሁም በምርጫ ያገኘውን ድምጽ በሚመለከት የሰራቸውን ስራዎች እና ጥንካሬዎች ለማጠናከር፤ በዚህ ሂደት የነበሩ ጉድለቶቾን በተመለከተ የሚፈቱበትን አቅጣጫዎች ጉባኤው ያስቀምጣል።
አሁን የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመሻገር የሚያስችል ብቁ አመራርና አሠራር ለማረጋገጥ የሚያስችል ጉዳዮችን በሚመለከት በዝርዝር ተወያይቶ ጠቃሚ ጉዳዮችን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል
የጉባኤው መሪ ሀሳብ “ከፈተና ወደ ልዕልና” መሆኑን እና ጉባኤው ኢትዮጵያ ወደ ከፍታዋ ለመውሰድ የተጀመረውን እንቅስቃሴ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ መሠረት እንደሆነም ገልጸዋል።
በመጨረሻም ይህን ጉባኤ ስኬታማ ለማድረግ መላው የከተማችን አባል በየደረጃው በሚከናወኑ የመሠረታዊ ፓርቲ ኮንፈረንሶች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።
ምንጭ፦ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት