የአዲስ አበባ ከተማ የህዝቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል አምራችን ከሸማች በቀጥታ ማገናኝት የሚያስችል የግብርና ምርቶች ማከማቻና መሸጫ ማዕከላት ግንባታ ፕሮጀክት ማስጀመርን ተከትሎ ግንባታው በታቀደለት የጊዜ ቀነ ገደብ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልፅዋል ፡፡
በአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽ/ቤት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሃንዲስ ጉርሜሳ ረታ (ኢንጅነር) እንደገለፁት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት አያት እና ወረዳ አምስት ሰሚት አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ለ16 ሰዓታት በመስራት፤ አስቸጋሪና ብዙ ጊዜ የሚወስደው የመሬት ውስጥ ግንባታ ስራ አጠናቆ ወደ ቀጣይ የግንባታ ምራዕራፍ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡
አስተባባሪ መሃንዲሱ አክለውም የፕሮጀከት ግንባታው በከተማው አስተዳደር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እና ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት አሁን ላይ ያለውን ህገወጥ የገቢያ ትስስር ሰንሰለትን ለማስቀረት እና የነዋሪውን ህብረተሰብ የኑሮ ጫና ለማቅለል እየተሰራ ያለ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡
ተቋራጭ ድርጅት ኦቪድ ግሩፕ ኮልፌ ሳይት ፕሮጀክት ማናጀር እንዲሁም የአመካሪ ድርጅት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ በበኩላቸው ለፕሮጀከቱ በተገባው ውለታ መሰረት ሰርቶ ለማጠናቅ በእቅድ የተቀመጠ መርሃ ግብር በመቅረፅና እና ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር በሁለት ፈረቃ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበለት ይህ ግዙፍ የከተማው አስተዳደር ፕሮጀክት ለከተማው ነዋሪ ህበረተሰብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ትልቅ የልማት አካል ነው፡፡