የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ለበዓሉ የምግብ ዘይት አቅርቦትን በተመለከተ ከዘይት አምራቾች፤አከፋፋዮችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
መጪውን የ2014 ዓ.ም አዲስ ዓመት እና ቀጣይ በዓላት በከተማዋ በቂ የምግብ ዘይት ምርት እንዲኖር ፣ የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ በማከለ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሰራጭ ውይይት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልፈታ የሱፍ ገልጸዋል፡፡
የዘይት አምራቾችና አካፋፋዪች በዚህ ወሳኝ ወቅት ለትርፍ ሳይሆን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድርግ ለመስራት እንዳለባቸው ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
የምግብ ዘይት አካፋፋዪችም ቢሮው በሚሰጣችሁ ድልድል መሰረት ከአምራች ድርጅቶች በመውሰድ ለህብረተሰቡ በፍጥነት ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው የገለጹት አቶ አብዱልፈታህ አስፈላጊውን ክፍያ ለአምራቾች በመክፈል በዓሉ ሳይደርስ ምርቱን ማሰራጨት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የዘይት አምራቾችን የወከሉት አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው የዘይት አምራቾች የህብረተሰቡን የዘይት ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ ከወትሮው በተጠናከረ መልኩ መዘጃጀታቸውን ገልጸው የዘይት አምራቾችም ሆኑ አከፋፋዮች ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ያለችበትን ፈተና ታሳቢ በማድርግ ለትርፍ ሳይሆን ያለውን የዘይት ምርት ለህብረተሰቡ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የሚመረተውንና ከውጭ የሚገባውን ጨምሮ በጠቅላላው ከ53 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለአዲስ ዓመት በዓል ለማድረስ እየሰራ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መግለፁ ይታወሳል፡፡