ከተማ አስተዳደሩ 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ እና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ሽፋን ህገወጥ የመሬት ወረራ እንዳይፋፋ አስቀድሞ ዝግጅት ተደርጎ መሰራቱን ገልፆል፡፡በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በከተማዋ በተፈጸመ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመቆጣጠር እየተወሰደ ባለው እርምጃ ዙሪያ ለመገኛኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በነበረው ብልሹ የአሰራሮች ምክንያት የመሬት እና በመሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ስር የሰደደ ውስብስብ ችግር መኖሩን አቶ ጥራቱ በየነ ገልጸዋል፡፡ከለውጡ ወዲህም በመሬት ዘርፍ የአደረጃጀት፣ የአሰራር ማሻሻያ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በተለይ የአርሶ አደሩን የአርሶ አደር ልጆችን በመሬታቸው ተጠቃሚ እንዲሆን አሰራሮች ተዘርተዋል፣ መመሪያዎች ጸድቀው ስራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡ነገር ግን አንዳድ ቡድኖችና ደላሎች በከተማዋ በተለይ በማስፋፊያ አካባቢዎች ህገ-ወጥ የመሬት ወረራዎችን የማካሄድ ሙከራዎችና ተግባራት እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ስራ አስኪያጁ በቅርቡም ካርታ ከወጣላቸው 2ሺ170 ይዞታዎች ውስጥ በተደረገ ማጣራት 497 ቦታዎች ወይም 207ሺህ ካሬ ሜትር (20.7 ሄክታር) ቦታ ከመመሪያ ውጪ ለሌላ አካል በህገወጥ ተላልፎ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በተለይ የመንግስትና የህዝብ ትኩረት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫን በሰላም ማጠናቀቅ፣ ሀገር ላይ የተከፈተውን የጦርነት የመቀልበስ፣ የህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት፣ የአዲሱን የመንግስት ምሰረታ ጨምሮ ትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚደረግ በመሆኑ በእነዚህ ወቅቶች ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ በመነሳት ወረራው እንዳይስፋፋ አስቀድሞ ለመከላከል ጠንካራ የክትትል፣ የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት የተለያዩ እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይቷል፡፡
በ2013 በዓመቱ መጀመሪያ የከተማ አስተዳደሩ ባደረገው የማጥራት ስራ ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ የመንግስት ቦታዎች ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ቢያደርግም 383.3 ሄክታር መሬት በድጋሚ መብት በሌላቸው አካላት እንደተያዘ እና በድጋሚ የማስመለስ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለአረንጓዴ ልማት ከተለዩ 252 ቦታዎች 35 የሚሆኑ ቦታዎች በግለሰብች መታጠራቸውና ይህንንም የከተማ አስተዳደሩ በሰራው የማጣራት ስራ ወደ ባንክ እንዱገባ ማድረጉንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በተያያዘም ለሃይማኖት ተቋማት እና ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በከተማ ተብሎ ካቢኔ ውሳኔ የተላለፈባቸው 70 ከሚሆኑ ቦታዎች መካከል 39ኙ በውሳኔው መሰረት አለመተላለፉን የገለጹት አቶ ጥራቱ ከነዚህም ውስጥ 19 የሚሆኑትን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የካቢኔውን ውሳኔ አለመተግበሩን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የመንግስት መሬት በህገወጥ መንገድ ሲያዝ በቸልተኝነት ፣ በጥቅም ትስስር መሬት እንዲወረር ያደረጉ አመራሮች ፣ባለሙያዎች እና ሌሎች አካላት ተለይተው በየደረጃው ተጠያቂ ማድረግ ስራ መጀመሩን አቶ ጥራቱ ተናግረዋል፡፡
በከተማ የመሬት ማኔጅመንት ቢሮ አመራሮች ጀምሮ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ድረስ በቀጥታ በብልሹ አሰራር ውስጥ የተሳተፉ ፣ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ከ120 በላይ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተለይተው ከስራ ማገድ ጀምሮ ጉዳያቸው በህግ እንዲጠየቁ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አቶ ጥራቱ አብራርተዋል፡፡
ህብረተሰቡም ህገወጥ ድርጊቶችን ለመላከል የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ጥፋጠኞችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው እንቅስቃሴ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ዋና ስራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡