የህብርት ስራ ማህበራት የሚስተዋሉባቸው ችግሮች ስር ነቀል በሆነ አግባብ ለመፍታት አላማ ያደረገ ከተማ አቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት የንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኤጀንሲ አማካኝነት በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኤጀንሲ አማካኝነት የተዘጋጀው ከተማ አቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት የንቅናቄ መድረክ በዛሬው እለት የተለያዩ አካላትና ባለድረሻ አካላት በተገኙበት የንቅናቄ መድረኩ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ በመርሀ ግብሩ ላይ እንደገለጽት በከተማዋ ከ8ሺህ በላይ የህብረት ስራ ማህበራት በተለያዩ ዘርፎች ተደራጅተው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ማህበራቶቹም የተደራጁበት የስራ አይነቶች የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ፤የመኖሪያ ቤት ህብርት ስራ ማህበራት፤የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ፤የከተማ ግብርና ህብረት ስራ ማህበራት፤የእደ ጥበብ ህብረት ስራ ማህበራት እና በሌሎች ዘርፍ የተደራጁ ያሉ ሲሆን በእነዚህ የህብርት ስራ ማህበራት በከተማችን ከሚገኘው ነዋሪ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ግለሰብ አባላት በእነዚህ የህብረት ስራ ማህበራት ታቅፈው እንደሚገኙ ገልፀዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በገንዘብ ቁጠባና ብድር አገልግሎት 1ሺህ 186 ህብረት ስራ ማህበራት በመደራጀት ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ በመቆጠብ የከተማውን ነዋሪ የቁጠባ ባህል እንዲዳብር በማድረግ ከተቆጠበው ለማህበሩ አባላት እና ለሌሎች ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ሌላው የከተማችን አንገብጋቢው ችግር የኑሮ ውድነት ሲሆን በተለይ በከተማችን 148 መሰረታዊ የሸማቾች ህብርት ስራ ማህበራትና 10 የሸማች ህብርት ስራ ዩኒየኖች በመጠቀም ከገጠር ከተማ የገበያ ትስስር በመፍጠር ለአባሉ ብሎም ለመላው የከተማችን ነዋሪ የግብርናና የግብርና ውጤቶችን ተደራሽ ለማድረግ የመሰረታዊ ሸቀጥ ስርጭት በከተማ ውስጥ ላሉ ከ30 ሺህ በላይ ቸርቻሪ ነጋዴዎች በጅምላ ሸቀጦችን በማቅረብ ወደ መላ የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲደርስ በማድርግ የኢንዱስትሪ ምርቶች ለተጠቃሚው በማቅረብ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም አቶ ግዛቸው ገልጸዋል፡፡
የህብረት ስራ ማህበራት በሀገራችንና በከተማ ለሚኖረን ሁለንተናዊ ብልጽግና የላቀ ሚና እንደሚኖራቸውም እሙን ነው፤ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ነገር ግን የኅብረት ስራ ማኅበራቱ የሚጠበቅባቸውን ሚና ከመወጣት አኳያ ለአባላቶቻቸውም ሆነ ለህዝቡ ከሚሰጡት አገልግሎት አንጻር ሲታይ ፤ የብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት ይነሳሉ እነዚህን የዘመናዊነት አሰራርና የአገልጋይነት ችግሮች ለመፍታት ህብረት ስራ ማህበራቱን በአሰራር፤ በአደረጃጀት ፤በግብአት ስር ነቀል ሪፎረም በማድረግ ህብረት ስራ ማህበራቱን ማስተካከል አላማ ያደረገ የንቅናቄ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህ ከተማ አቀፍ የህበረት ስራ ማህበራት የንቅናቄ መድረክ እስከ ታች የሚገኝ የመንግስት አመራር አካላት ከፍተኛ ድጋፍ ከታከለበት በማህበራቱ በኩል የሚታዩ ጉድለቶች ለማረም እና ማህበራቱን ለተሸለ አገልግሎት ለማብቃት ጉልህ ሚና ስለሚኖረው በተለይ በየደረጃው የሚገኝ አመራር ይህንን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡