ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን የማይናወጥ አቋም በየጊዜው ስትገልፅና ይህንኑ አቋሟን በተግባር ስታረጋግጥ መቆየቷ የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡
ሆኖም ስለሰላም የተዘረጉትን እጆች አሻፈረኝ በማለት ለ3ኛ ዙር በሃገራችን ላይ የጥፋት በትሩን የዘረጋው አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተውን ጦርነት ተገደን ለመመከት ወደመከላከል መግባታችን ይታወቃል፡፡
የህወሓት አሸባሪ ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጰያውያን ላይ ተነግረው የማያልቁ እልፍ አዕላፍ መከራና ሰቆቃ ሲፈፅም የኖረ እኩይ እና ፀረ ህዝብ ቡድን በመሆኑ የጭካኔ በደሉ በበረታባቸው ኢትዮጵያውያን የጋራ ክንድ ከስልጣን የተወገደው ይህ የአሸባሪ ስብስብ አሁንም ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር አብሮ አገራችንን የማፈራረስ ግብ አንግቦ ወረራ ፈፅሟል፡፡
ሆኖም በጀግናው የመከላከያ ሰራዊቻችንና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አኩሪ ተጋድሎ የአሸባሪው ቡድን የጥፋት ላንቃ እየተዘጋና ወረራውን በብቃት እየተመከተ ይገኛል፤ ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትልቅ ክብርና አድናቆት አለው፡፡ ምንጊዜም ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን መሆናችንን በተግባር እያረጋገጥን ሃላፊነታችንን በብቃት እንወጣለን፡፡
በተመሳሳይ ዛሬም እንደ ትናንቱ በጦርነቱ ግንባር የአማራና የአፋር ንፁሃን ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከልና ጉዳት የደረሰባቸውን ለመደገፍ ያለንን ቁርጠኝነት ተግባራዊ በማድረግ እንቀጥላለን፡፡
ይህ እኩይ ቡድኑና ተላላኪዎቹ አልሆነላቸውም እንጂ በተደጋጋሚ አዲስ አበባንም ለማተራመስ የሽብርና የእርስ በእርስ እልቂት ውስጥ ለመክተት የማያባራ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ይህንኑ ቅዠታቸውን ለመፈፀም ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡
በተለይም በሃሰት ፕሮፖጋንዳ፤ ህዝብ ከህዝብ የሚያጋጩና አንድነታችንን የሚበትኑ የተፈበረኩ መረጃዎችን በማሰራጨት ፤ በከተማዋ ውስጥ የሽብር ቡድኖቹ የህወሓትና የኦነግ ሸኔን የተለያዩ የፅንፍ አስተሳሰብ የሚረጩ አባላትን በማስረግና የጥፋት ሴሎችን በማደራጀት ፤ ሰላማችንን ለማወክ፤ የጸጥታ ስጋት ለመፍጠርና የእኩይ እቅዳቸውን ለማሳካት በግልጽ እንቅስቃሴ እያካሄዱ ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለረጅም ዘመናት በዘረጋው የሌብነትና የዝርፊያ አደረጃጀቶችና አሰርጎ ባስገባቸው ተላላኪዎች ተጠቅሞ በተለያዩ ወንጀሎችና የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈፀም፤ ህብረተሰቡን በማማረር መንግስት ላይ ጫና ማሳደር በሚለው ያረጀ ስልት ለመጠቀም ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ከእነዚህ ስልቶችም መካከል፤ በየቦታው ህገ ወጥነትን ማስፋፋትና የመሬት ወረራ እንዲካሄድ በማድረግ፤ የፖለቲካ ግብ ያላቸው የደረቅ ወንጀሎች እንዲስፋፉ በማድረግ፤ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም የኑሮ ውድነት እንዲባባስና ህዝቡ አንዲማረር ለማድረግ የቀን ቅዠታቸውን ለማሳካት ግብ ያደረጉ እንቅስቃሴዎቻቸው በየአካባቢው መታየት ጀምረዋል፡፡
ይህ ከህዝብ ልብ ተተፍቶ የወጣ ሃይል ፤ በህዝብ ውስጥ ሊሸሸግ የሚስችለው አንዳችም እድል እንደሌለው የታወቀ ቢሆንም በማናቸውም ሁኔታ የዚህ እኩይ ተግባር ተሳታፊ ሆነው ያገኘናቸው አካላትም ሆኑ ሰዎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ የምንወስድ ይሆናል፡፡
የከተማችን ነዋሪዎችም ወቅታዊ የኑሮ ጫናን ለማቃለል ለበዓል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የከተማ አስተዳደሩ በበቂ ሁኔታ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል እንዲቀርብ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን በማወቅ ፤ ለህገወጦች እቅድ ተጋላጭ ከመሆን ራሱን እንዲጠብቅ ማሳሰብ እንወዳለን!
በተለይም ቀጣዮቹ ሳምንታት በርካታ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት በመሆኑ እነዚህ በአላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የከተማችን ነዋሪ ልክ እንደከዚህ ቀደሙ አካባቢውን ብሎም ከተማውን በንቃት ተደራጅቶ እንዲጠብቅ ፤ ከፀጥታ ሃይሉ እና ከሰላም ሰራዊቱ አደረጃጀት ጋር በመተባበር እንዲንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በየአካባቢው በህገወጥ ድርጊት የተሰማሩ፤ ፀጉረ ልውጦችን፤ የሽብር ወሬ የሚነዙና የኢኮኖሚ አሻጥር ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም የተለያዩ ህዝባዊና መንግስታዊ አገልግሎቶች እንዲስተጓጎሉ የሚያደርጉ አካላትን ለፀጥታ ሃይሉ በመጠቆም እንዲሁም በማጋለጥ አገራዊ ሃላፊነታችንን እንድንወጣም የከተማ አስተዳደሩ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
በመጨረሻም የከተማችን ህዝብና አስተዳደር ከግንባር እስከ ደጀን ለሰራዊታችን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን እያረጋገጥን ፤ ሁላችንም በየተሰማራንበት ውጤታማ በመሆን የእኩይ ሴራዎችን እያከሸፍን ፤የመዲናችንን ሰላም ዘላቂነት በማረጋገጥና ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ በተደራጀና በተቀናጀ አመራርና ከህዝባችን ጋር እጅና ጓንት ሆነን መስራትን አጠናክረን የምንቀጥል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡
እውነትና ሃቅ ከኢትዮጵያ ጎን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የያዘቸውን ምንጊዜም የማይናወጥ የፍትሃዊነትና ፤የሰላማዊነት አቋም የአሸናፊነት ጋሻዎቻችን ናቸው፡፡
ከሩቅ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እስከ ቅርብ ባንዳዎች ድረስ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ፣ የሞከሩት ሁሉ አሸንፈን መልሰናቸዋል። ዛሬም እንመልስላቸዋለን!!
አዲስ አበባ በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብርና አንድነት ሃላፊነቷን በብቃት ትወጣለች!!
ኢትዮጵያ ድል እያደረገች ትቀጥላለች!!
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር