በዛሬው እለት ከፊታችን የሚመጣውን የመስቀል በዓል እና ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ በሁሉም የክ/ከተሞች ህዝባዊ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
በተለይም በዓሉ በሚከበርበት የቂርቆስ ክ/ከተማ በተካሄደው ውይይት ህብረተሰቡ በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ሁሉም ሃላፊነቱን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም በዓሉ ለሃገራችን መገለጫ ከሆኑ በዓላት አንዱ በመሆኑ በከፍተኛ ድምቀት ሃይማኖታዊና ህዝባዊ እሴቶቹን ጠብቆ እንዲካሄድ ሁሉም ነዋሪ የበኩሉን እንደሚወጣና አጠራጣሪና የፀረ ሰላም ሃይሎችን እንቅስቃሴ በመከታተል ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሆን ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በመድረኩ የተገኙ ተደሳታፊዎች ጠቁመዋል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ ተገኝተው ያወያዩት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት ይህንን በኣል የምናከብረው አሁን ፀረ ሰላም ሃይሎች በጦርነት የደረሰባቸውን ኪሳራ በተላላኪዎቻቸው አማካኝነት አዲስ አበባ ላይ ለመመለስ ርብርብ በሚያደርጉበት ሰዓት ነው ብለዋል፡፡
እነኚህ በአለም ኢትዮጵያን ያስተዋወቁ በዓላት የስበት ማእከል በመሆናቸው እንደ ትልቅ እድል ለመጠቀም እየሞከሩ ነው፡፡ ይህም ግምት ሳይሆን በተጨባጭ ማሳያዎችን በየሚድያው እያያችሁ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ሆኖም ህዝቡ በየአካባቢው መፈናፈኛ አሳጥቷቸዋል፤ አሁንም እኛ ክፍተት ካልሰጠናቸው በስተቀር ምንም አይነት መንገድ የላቸውም ፤ ለዚህ ደግሞ በህዝባችን ላይ እምነት አለን ብለዋል፡፡
ጦርነቱን ዳግም የምናሸንፋቸው በዓሉን ሰላማዊና ደማቅ አድርገን በማክበር ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች እነኚህ ሴረኞች ምንም እድል አይኖራቸውም ብለዋል፡፡
በእምነት በብሄር በአካባቢ እንደተካፋፈልን አስመስለው ለአለም ማሳየት ለሚፈልጉ ሃይሎችም አንድ ሆነን በዚህ በዓል አንድነታችንን ለአለም እናሳያለን!!
በአሉ እጅግ በጣም ያማረ ትውፊት ያለው በዓል ስለሆነ እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ ከክብሩ ሳይጎድል እንዲከበር ተባብረን እንስራም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም ህብረተሰቡ ለፀጥታ ሃይሎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በጋራና በትብብር እንዲሰራም አሳስበዋል፡