በመላው አዲስ አበባ የበጎ ፍቃድ ቀንን ምክንያት በማድረግ የማእድ ማጋራት የተከናወነ ሲሆን ይህ በአጠቃላይ በገንዘብ ሲሰላ በጥቅሉ 365ሚ 658 ያህል መጠን ያለው ማእድ ተጋርቷል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የማዕድ ማጋራት ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት በዛሬው ዕለት የበጎ ፈቃደኝነትን ቀን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ያለንን ፍቅር፣ አብሮነትና ዘላቂ አጋርነት በተግባር ለማረጋገጥ በአሥራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የማዕድ እናደርጋለን ብለዋል ።
ከተማ አስተዳደሩ በየግዜው የአቅም ደካማ ወገኖችን ኑሮ የሚያቃልሉ ሥራዎችን በዘላቂነት ይሰራል ለዚህም የተባባሪ አካለትን ያልተቋረጠ ድጋፍ ይሻል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ።
የቅዳሜና እሁድ ገበያን ጨምሮ መካከለኛ ገቢ ያላቸውና አቅም ደካማ ወገኖችን ለመደገፍ ከተማ አስተዳደሩ ከአቅራቢዎችና ከክልሎች ጋር በቅንጅት ይሰራል ለዚህም ቁርጠኛ ነው ሲሉ ገልጸዋል ።
የአገራችን ሁለንተናዊ ክብር የሚለካው የእያንዳንዱ ዜጋ ተጠቃሚነትና ክብር ሲረጋገጥ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለዜጎች የኑሮ መሻሻል ሁላችንም በየደረጃው ማህበራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል ክብርት ከንቲባዋ ።
እኛ የምናካፍላችሁ ማዕድ ብቻ ሳይሆን ለናንተ ያለንን ፍቅርም ጨምር ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ድጋፍ በሚያስፈልጋችሁ አቅጣጫ ሁሉ ከተማ አስተዳደሩ በአጋርነት አብሯችሁ ይቆማል ብለዋል ።
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን አሁን ባለንበት ወቅት ሕይወቱን እየሰጠ አገራችን ያላትን ሃብት ለእናንተ እንድናከፍል ረድቶናል ያሉት ከንቲባ አዳነች እኛም አስፈላጊ በሆነው ሁሉ ሰራዊታችንን በመደገፍ የአገራችንን ሉአላዊነትና የሕዝባችንን አንድነት ልናጸና ይገባልም ብለዋል ።
ከጸጥታ አካላትና ተቋማት ጋር በቅንጅት አስቀድመን ስናደርግ እንደነበረው የከተማችንን ሰላም በጠበቅ ልማታችንን ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል ከንቲባ አዳነች ።