በከተማችን በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የኦሮምያ ባንዲራ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ ያጋጠሙንን የፀጥታ ማደፍረስ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ በዛሬው እለት በግልፅ ተወያይተናል፡፡
እንደሚታወቀው የኦሮሞ ህዝብ በአፋን ኦሮሞ እንማር የሚለው ጥያቄን በለውጡ ዋዜማ (በዘመነ ኢህአዴግ) እና የለውጥ እንቅስቃሴ በወቅቱ ለነበረው ውጥረት ምላሽ እንዲሆን በጥድፊያ የተጀመረ ሲሆን በአጠቃላይ ከተጀመረ በከተማችን 5 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
በወቅቱም አፋን ኦሮሞ ቋንቋን ለማስተማር ሲፈለግ ለዚህ የሚሆን ስርዓተ ትምህርት የአዲስ አበባ ከተማ ስላልነበራት የአፋን ኦሮሞ ማስተማርያ ስርዓተ ትምህርት ከኦሮምያ ክልል በውሰት የተወሰደ ሲሆን በስርዓተ ትምህርቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ትምህርት ሲሰጥ የክልሉ ባንዲራ እንዲሰቀልና የክልላዊ መንግስቱ መዝሙር መዘመርን አያይዞ በአንድ ላይ እንደ ህግ የሚያስቀምጥ በመሆኑ ይህ ሁኔታ ትምህርቱ በሚሰጥባቸው አካባቢዎችም ሁሉ ላለፉት አመታት ሲተገበር ቆይቷል፡፡
ነገር ግን በአንዳንድ አካላት ዛሬ እንደተጀመረ አስመስሎ በማቅረብና የአንድን ክልል ባንዲራና መዝሙር በተለየ ሁኔታ በግድ ለመጫን እንደተደረገ አስመስለው በማቅረብ እየፈጠሩት ያለውን ውዥንብር ትክክል አለመሆኑን በዛሬው ውይይታችን ከህብረተሰቡ ጋር በግልፅ ተማምነናል ፡፡
ሆኖም ይህ አጀንዳ ከአንድ አመት በፊት ለአዲስ አበባ ምክር ቤት በቀረበው ሪፖርት መሰረት አዲስ አበባ አፋን ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን በሶማሊኛና ጋሞ ቋንቋም ማስተማር ስለጀመረች እና ተጨማሪ ቋንቋዎችንም ለማስተማር የጀመረችው የስርዓተ ትምህርት ጥናት በመጠናቀቁ፤ ይህ የግጭት አጀንዳ መሆን የለበትም በሚል ቀርቦ ሃሳብም ተሰጥቶበት ነበር፡፡
አሁንም በምክር ቤቱ ላይ ቃል ገብተነው እንደነበረው ለአዲስ አበባ የተዘጋጀውን የቋንቋዎች ስርዓተ ትምህርት ጥናቱ አጥንተን ያጠናቀቅንና ወደ ውሳኔ እየመጣን በመሆኑ ህብረተሰቡ እና የትምህርት ማህበረሰቡ በእርጋታ ከጥፋት ሃይሎች ሴራ ራሱን እየጠበቀ እንዲቆይ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
በተለይም አምስት አመታትን የቆየ አጀንዳ ልክ ዛሬ አመራሩ ያመጣው አዲስ ጉዳይ በማስመሰልና ፤አንዱ ብሄር በሌላው ላይ የበላይነት ለማምጣት እየተሰራ እንዳለ በማስመሰል የሚቀርበው ሃሳብ ፤ ፍፁም የተሳሳተና የፅንፈኛና አሸባሪ ሃይሎች ፤ በዚህ አጀንዳ ከተማችንን ለማተራመስ እየሰሩት ያሉት ጉዳይ መሆኑንም ከውይይቱ ተሳታፊዎች ጋር ተስማምተናል፡፡
አሁንም ቢሆን ማንኛውንም አይነት ጥያቄና ሃሳብ በመመካከርና በውይይት እንጂ በሁከትና በትርምስ መሆን እንደሌለበትም መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡
በመሆኑም ሰላማዊ የመማር ማስማር ሂደቱ እንዳይስተጓጎልና የከተማችን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ግባችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እነዚህን የግጭት ነጋዴዎች አጋልጦ የመስጠት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆን ይኖርበታል፡፡
መንግስትም የህግ የበላይነትን ለማስከበር፤ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ!!
ውድ ተማሪዎቻችን ለጥያቄው በህጋዊ አካሄድ ምላሽ እንደሚሰጥ አውቃችሁ፤ እስከዛው ድረስ መላው ትኩረታችሁን ሰብስባችሁ ትምህርታችሁ ላይ እንድታደርጉ በትህትና እጠይቃችኋለው።
መንግስታዊ ሃላፊነታችንን የህዝባችንን ስሜትና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ሁሉንም ጉዳዮች በቅርበት ከህዝቡ ጋር እየተመካከርን መወጣታችንን እንቀጥላለን!!
አዲስ አበባ በህዝቦቿ የጋራ ትብብር እንደ ስሟ አዲስ ውብና አበባ ትሆናለች!!
የጋራ ቤት በእልህ በፉክክር በመከፋፈል አይገነባም፤ ሁላችንም በጋራ እንቁም ፤የግጭት ነጋዴዎችን ቦታ አንስጣቸው!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!!”
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ