በዛሬው እለት የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት የትንሳኤ በአልን በአዲስ አበባ ስታዲዬም በደማቅ ሁኔታ አክብረዋል ።
የወንጌል አማኞች ህብረት ፕሬዘዳንት መጋቢ ፃዲቁ አብዶ በበአሉ ላይ እንደተናገሩት ትንሳኤ መከራን፤ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታና ጨለማን ተሻግሮ ወደ አዲስና የሚደነቅ ብርሃን መግባትን፤ በአሸናፊነት መውጣትን የሚያመለክት የድል ብስራት ነው ያሉ ሲሆን
ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ: የሞተው ሃጥያት ወይም በደል ተገኝቶበት ሳይሆን ስለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅር ሲል ነው፡፤ በዚህ ታላቅ የፍቅር ተምሳሌትነቱን ማሰብ ና መቀጠል አለብን ብለዋል::
በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የትንሳኤው ትርጉም በራሳችን ላይ ለውጥ እንዲያመጣ መፍቀድ አለብን ብለዋል።
በትንሹ ፍቅርን በማካፈል ፤ሁሉን ሰው ሳናዳላ በእኩል አይን በመመልከት በፍትሃዊነት በማገልገል፤ በይቅር ባይነት ብንበደል እንኳን በምህረት በማለፍ ፤ ሌሎችን በመውደድ የትንሳኤውን ትርጉም በተግባር እንቀይር ብለዋል::
አክለውም እኛ ኢትዮጵውያን በመካሰስና ጣት በመጠቋቆም : ተራርቀንና ተነጣጥለን ልናሸንፍ አንችልም፡፤ አንዱ ተጎድቶ ሌሎቻችን ልንጠቀም አንችልም ፤ አንዱ አዝኖ ሌሎቻችን ልንደሰት አንችልም:: ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ የጋራ ጉዳያችን ጥቅሞቻችን የተሳሰሩ ስለሆኑ ተከባብረን እየተሳሰብን ተከባብረን በጋራ እንስራ ብለዋል::
በመጨረሻም በዓሉ በዝማሬ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነስርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።