በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዘጋጅነት በመከበር ላይ ባለው የጳጉሜ ቀናት የአዲስ አመት መቀበያ መርሐግብር #ማገልገልክብርነው በሚል እየተካሄደ ባለው የአገልጋይነት ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት “አገልጋይነት ታላቅነት ነው። ክብር የሚገኘው ከማገልገል ነው። ፈጣሪን፣ ሀገርን፣ ሕዝብን፣ ከማገልገል ውጭ ምን ሕይወት አለ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ሁላችንም በአንድ ቦታ አገልጋዮች በሌላም ቦታ ተገልጋዮች ነን ያሉት ዶ/ር አቢይ አገልጋይነት የሁላችንም ባህልና ሥነ ምግባር ከሆነ የትኛውም መስሪያ ቤት መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ይሆናልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ” አገልጋይነት የሆኑ አካላት ብቻ እንዲያገለግሉን ከጠበቅን ግን በአንዳንድ ቦታዎች ተፈልጎ የሚገኝ ብርቅ ሀብት ይሆንብናል ሲሉ ሀሳባቸውን አስፍረዋል።
በቂና ብቁ አገልጋዮች የሌሏት ሀገር፣ በዕድገት መራቅና መምጠቅ እንደሚቸግራትም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አስታውሰዋል።