15ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ ይውላል፡፡ ቀኑን ስናከብር በደም ጠብቀን ያቆያናትን ሀገራችንን በደማችን እና በላባችን እያጸናን ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር ምልክት ነው። ይሄንን ዓርማ ይዘው ጀግኖች መሥዋዕትነት ከፍለዋል። በዓለም አደባባይ አሸንፈዋል። ይህ ሰንደቅ ዓላም ከልጅ እስከ ዐዋቂ ልብ ውስጥ የማይፋቅ ማኅተም አሳርፏል።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የትናንት የጋራ ታሪካችንን፤ የዛሬ ጥረታችንን እና የነገ ተስፋችንን እንዲሁም ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን አጣምሮ የያዘ የክብራችን እና የማንነታችን ማኅተም ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ሰንደቅ ዓላማዋን አንግበው ለሉዓላዊነቷ እና ለአንድነቷ የተዋደቁ የጀግኖች ልጆች እናት ናት፡፡ አሁን ባለንበት ዘመንም ቢሆን ሰንደቅ ዓላማዋን አንግቦ፣ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ የተነሡ ጠላቶቿን አሳፍሮ የሚመልስ ትውልድ ያላት፣ የእልፍ ጥቁር አንበሶች ምድር ናት፡፡ የቅርብ እና የሩቅ ጠላቶቻችን ከሀገር ውስጥ ባንዳ አሸባሪዎች ጋር ተባብረው ኢትዮጵያን ለመበታተን መሄድ እስከሚችሉት ድረስ ተጉዘዋል፡፡ ሆኖም በልጆቿ ደምና ብርታት ምኞታቸዉ ቅዠት ሆኖ ቀርቷል፡፡ እኛ ካልመራናት ትፍረስ ብለው፣ በየአካባቢው ግጭት ጠንሰሰው፣ ጠብን ስፖንሰር አድረገው ሕዝባችንን ተስፋ ለማስቆረጥ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡
እያንዳንዱ የሀገር ብተና ሤራቸው ተራ በተራ ሲከሽፍባቸው ደግሞ ሀገር ጠባቂ መከላከያ ሠራዊታችንን በሌሊት አጥቅተው ጦርነት ከፍተውብናል፡፡ ይህ ሁሉ ወጥመድ ግን ለሰንደቃቸው ክብር በሚሠዉ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች የጋራ ርብርብ ከግቡ ሳይደርስ መክኖ
ቀርቷል፡፡
በተለይም የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች በሀገራችን ላይ ጦርነት የከፈቱ አሸባሪዎችን ድል ነሥተው፤ ሀገራቸውን ከመፍረስ ታድገዋል፡፡ በደማቸው ሰንደቅ ዓላማችንን አስከብረዋል፡፡
ጠላቶቻችን ጦርነት የከፈቱብን ሁሉንም ትኩረታችንን ወደ ጦር ግንባር አድርገን በሌሎች ዘርፎች ሽባ እንድንሆን አስበው ነበር፡፡ ዓላማቸው ኢትዮጵያን አዳክሞ ማፍረስ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ዓላማቸው በቁርጥ ቀን ልጆቿ ብርታትና እና በሕዝባችን ድጋፍ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ “በደማችን እየጠበቅን በላባችን እናጸናለን” በሚል ዕሳቤ፤ የኢትዮጵያ ልጆች ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድ እጃቸው እያረሱ፤ በሌላኛው እጃቸው እየተኮሱ ሀገራቸውን እየገነቡ ነው። በአንድ በኩል ከጠላት እየተከላከሉ፣ በሌላ በኩል የሰብል ምርታቸውን በብዙ እጥፍ አሳድገዋል፡፡ በዚህ ሂደትም ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የግብርና ምርቶችን በማምረት፤ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ወደላቀ ምዕራፍ በማድረስ እና ሌሎቹንም በማጠናቀቅ ሕዝባችንን ተስፋ ሊያስቆርጡ የተነሡ ጠላቶቿን ተስፋ አስቆርጣለች፡፡ በዚህም የሀገር ክብርና ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት የልማት ሥራዎችን እያጧጧፉ ጎን ለጎን የተከፈተባቸውን ጦርነት ሲመክቱ፤ ዐዋቂ እና ወጣት አትሌቶቻችን ደግሞ በዓለም አደባባይ በሀገር ፍቅር ስሜት ተናበው የሀገራቸውን አሸናፊነት ለወዳጅም ለጠላትም ዐውጀዋል፡፡ ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርገው አውለብልበዋል፡፡ ከሀገር አልፈው የአፍሪካ ኩራት ሆነዋል፡፡
ኢትዮጵያችን በብዙ ፈተና በተወጠረችበት በዚህ ወቅት ጠላቶቿን እየመከተች የልማት ሥራዎችን በታላቅ ስኬት ቀጥላበታለች፡፡ የምግብ ሉዓላዊነት ሳይኖር የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር ከባ