በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉለሌ ክፍለ ከተማ በተያዘው በጀት ዓመት ሰርቶ ለማጠናቀቅ የተያዙ 17 የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።
ፕሮጀክቶቹን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፣ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቆንጂት ደበላ እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በተገኙበት ነው የተመረቁት።
የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያ፣ የወረዳ አስተዳደር ህንፃ ማስፋፊያ፣ የዳቦ መጋገሪያና ሌሎችም ፕሮጀክቶች ለምረቃ ከበቁት መካከል ይገኙበታል።
ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ 171 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉም ተነግሯል።
ማህበሩን በማሳተፍ ደግሞ ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ 108 ፕሮጀክቶችን ደግሞ ከህብረተሰቡ እና ከአጋር አካላት በተገኘ 85 ሚሊየን ብር መገንባት መቻሉ ተገልጿል።
የኮሚኒቲ ሴንተር ግንባታ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ድልድይ እና 104 የአቅም ደካማ ቤቶች እድሳት ያካተተ ሲሆን ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውም ተነግሯል።
በተጨማሪም የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል ግንባታን ለማከናወን የሚያስችል ቦታ ርክክብም ግንባታውን ስፖንሰር ላደረገው ኬዌይ ካምፓኒ ለቤተ-እስራኤል ብሪቶለም ተደርጓል።
ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ሁሌም ቁርጠኛ ነው ብለዋል።