በየካ ክፍለ ከተማ በጎዳና ላይ የንግድ ተግባር ሲያከናውን የነበረ ግለሰብ 10 ሺህ ሃሰተኛ ብር ይዞ በመገኘቱ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር የዋለው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ቦታው መገናኛ ተርሚናል አካባቢ ነው፡፡
ግለሰቡ በአካባቢው ላይ የጎዳና ላይ የንግድ ተግባር የሚያከናውን መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ህብረተሰቡ በጥርጣሬ የተመለከተውን ጉዳይ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠቱ በወንጀል መከላከል ስራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ሊያዝ መቻሉ ተገልጿል፡፡
በግለሰቡ ላይ በተደረገ ፍተሻም በባለ ሁለት መቶ የብር ኖት አስር ሺህ ሃሰተኛ ብር ይዞ በመገኘቱ ምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራትን በመፈፀም በሃገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ለማድረስ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መካከል የሃሰተኛ ገንዘቦች ዝውውር አንዱ ነው።
በተለይም በበዓላት ወቅት የሚኖረውን ግብይት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሃሰተኛ ገንዘብ ለማዘዋወር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ፖሊስ የሚያከናውነውን የቁጥጥርና ክትትል ስራ በመደገፍ ነጋዴውም ሆነ ሸማቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ፖሊስ አሳስቧል።
ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።