የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በደረሳቸው ጥቆማ ባደረጉት ብርቱ ክትትል ሦስት ግለሰቦች በኮድ 1-31917 አ.አ በሆነ ቢጫ ታክሲ አይነቱ 25 ቱርክ ሰራሽ ኢኮልፒ ሽጉጥ ፣ 586 ፍሬ የኢኮልፒ ሽጉጥ ጥይት ፣ 69 ፍሬ የብሬን ጥይት በጥቁር ገበያ በመገበያት ላይ እንዳሉ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ዘነበወርቅ አካባቢ ሀምሌ 28 ቀን 2013 ዓ/ም እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና ሀምሌ 23 ቀን 2013 ዓ/ም አንድ ግለሰብ 7 መቶ 30 ፍሬ የክላሽንኮቭ ጥይት ከገብስ ጋር በመቀላቀል ወደ ደቡብ ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስልጤ ዞን ለማዘዋወር ሲሞክር ዘነበ ወርቅ መናኽሪያ ውስጥ በጫኝና አውራጅ ስራ በተደራጁ ሰራተኞች ግለሰቡ ከእነ ጥይቱ መያዙን ፖሊስ ጨምሮ ገልፇል፡፡
በጥቁር ገበያ የጦር መሳሪያ ሲገበያዩ የተገኙት ሦስት ተጠርጣሪዎችና የክላሽንኮቭ ጥይት ሲያዘዋውር የተገኘው ግለሰብ ታስረው ጉዳያቸው እየተጠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ህገ ወጦች ልዩ ልዩ ስልቶችን በመጠቀም የጦር መሳሪያ እና ጥይት ለማዘዋወር እንደሚንቀሳቀሱ ነገር ግን የፀጥታ አካላት በሚያደርጉት ብርቱ ክትትል አብዛኞቹ እጅ ከፍንጅ እየተያዙ እንደሆነ እና ህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ የአውቶቢስ መናኸሪያ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ አበረታች ስልሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልእዕክት አስተላልፏል፡፡