ፖሊስ ህግን አክብሮ ማስከበር እና በተለይም የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ በትኩረት መስራት ያለበት ቢሆንም በአንዳንድ የፖሊስ አባላት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈፀሙ ተስተውሏል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ በመብት ጥሰቶች እና በሌሎች ወንጀሎች ላይ የሚሳተፉ አመራርና አባላቱን በተቋሙ የስነ-ምግባር ደንብ እና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግን ለአፍታም ቸል የሚለው ጉዳይ አይደለም፡፡
አንዳንድ የፖሊስ አባላትና አመራሮች በጀግንነት መጠበቅ በሰብዓዊነት ማገልገል የሚለውን የፖሊስ ተቋም መሪ-ቃል በመተላለፍ የሚፈፅሙት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ የሚገኘውን ብዙሃኑን የፖሊስ አመራር እና አባል የሚወክል እንዳልሆነም ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
በቅርቡ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በአንድ ተማሪ ላይ የድብደባ ወንጀል የፈፀሙ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው በህግ አግባብ እንዲጠየቁ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ይህንን መነሻ በማድረግ ከለውጡ በፊት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ ከመቀየሩ አስቀድሞ የተፈፀመን እና የእርምት እርምጃ የተወሰደበትን ድርጊት በቅርብ የተፈፀመ በማስመሰል በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ይገኛል፡፡ የቆዩ ምስሎችን በመለጠፍ ስህተትን ለማጉላት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በህዝብ እና በፖሊስ መካከል ያለው መልካም ግንኙነት እንዲሻክር የራሳቸውን ጫና የሚፈጥሩ በመሆኑ ይህንን ህገ ወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ፖሊስ እያሳሰበ ሆኖም ህገወጥ ተግባር ሲፈፀም ያየና ማስረጃ ያለው ማንኛውም አካል ማስረጃውን ለተቋሙ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ እየጠየቀ ተቋማችን ከህብረተሰቡ በልዩ ልዩ መንገዶች የሚደርሱትን መረጃዎች መነሻ በማድረግ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ ይገልፃል፡፡