ግንባታው በደቡብ ግሎባል ባንክ የሚከናወን ሲሆን የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሩሳ ፣ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ብሩክ ከድር እንዲሁም የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ቦሩ በይፋ አስጀምረውታል።
ቦታው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ከቄራዎች ድርጅት ፊት ለፊት ያለው ሰፊ ቦታ ሲሆን በአጭር ቀናት ውስጥ በዘመናዊ መልኩ ተገንብቶ ለህዝብ አገልግሎት እንደሚውልም የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ብሩክ ከድር ተናግረዋል።
ቂርቆስ ፓርክን በይፋ ያስጀመሩት የደቡብ ግሎባል ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት የሚፈጥረውን ይህንን ፓርክ ለማስገንባት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው ይህ ፓርክ የሁላችን ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ በፍጥነት እያደገች ያለች ከተማ ስለመሆኗ ትልቅ ማሳያ ነውና በጋራ ተረባርበን በማጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት እንዲውል እናደርጋለን ብለዋል።
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአዲስ አበባ እምብርት በመሆኗ እንዲህ ያሉ ታላላቅ ግንባታዎች ያስፈልጓታል ያሉት ዶክተር ቢቂላ ቂርቆስን በማልማት ሂደት ትልቁን ኃላፊነት የወሰደው ደቡብ ግሎባል ባንክና የክፍለ ከተማው አስተዳደር ሊበረታታ ይገባልም ብለዋል።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊነት መለኪያ ፣የሁሉም ዜጋ ቤትና የሁሉም ሰው አብራክም ነች ብለዋል ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በመልዕክታቸው።
የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ቦሩ ግንባታው ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ገልፀው ክፍለ ከተማው ፍቃደኛ ሆኖ ስለሰጠን እኛም በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቀቅ ለህዝብ አገልግሎት እንዲውል እናስረክባለን ብለዋል።
የቂርቆስ ፓርክ ግንባታው ሲጠናቀቅ የተለያዩ ከመዝናኛነቱ ባሻገር ፣ የንባብ ቦታዎች ፣ የህፃናት መጫዎቻዎች፣ የሻይ ቡናና የፋስት ፉድ አገልግሎቶች፣ የህዝብ መፀዳጃና ሌሎች ስራ ዕድሎችን እንደሚፈጥርም ዶክተር ብሩክ ገልፀዋል።
ይህ ለህዝቦች ተጠቃሚነት ትልቅ ፋይዳ ያለው ሰው ተኮር ግንባታ ተጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት እስኪውል ድረስ የቄራ አካባቢ ነዋሪዎች ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ይጠብቁ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ዶክተር ብሩክ ከድር