አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ በማይሰጡ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡና የትራንስፖርት አገልግሎት በሚያቋርጡ ተሽከርካሪዎችና አሽከርካሪዎች ላይ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ፡፡
ቢሮው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በላከው መግለጫ ፥ ከነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት ድጋፍ ሰጪዎችን ጨምሮ በተመደቡበት የስምሪት መስመር በመገኘት በተቀመጠው የታሪፍ መጠን ብቻ አገልግሎታቸውን መስጠት እንደሚገባቸው ገልጿል፡፡
በጥናት መመለስ የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉም ቢሮው አሰራሩን በመፈተሽ በሂደት ምላሽ እንደሚሰጥም ነው የገለጸው፡፡
በሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በኪራይ ውል አገልግሎት የሚሰጡ ድጋፍ ሰጪዎች ከቢሮው ጋር በገቡት ውል መሠረት የትራንስፖርት አገልግሎት የማይሰጡትን ቢሮው ከስምምነት ውል ውጪ እንደሚያደርጋቸው አውቀው ወደነበሩበት መስመር በፍጥነት እንዲገቡ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በ11ዱም የትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ባሉ መስመር በማይሸፍኑ ፣ ህብረተሰቡን ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ፣ መስመር በሚያቆራርጡ፣ የመስመር ታፔላ በማይሰቅሉ /ከእይታ ውጪ በሚያደርጉ/ ፣ ታሪፍ በማይሰቅሉ /በማይለጥፉ/፣ አሽከርካሪዎችን ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጪ የሚያውሉ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች ካሉ ከወዲሁ ጥብቅ ጥንቃቄ በማድረግ በአግባቡና በተገቢው መንገድ ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ ነው ቢሮው ያሳሰበው፡፡
በዚህም ህግና መመሪያዎችን ተከትለው በማይሰሩ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች ላይ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድም ነው በጥብቅ ያሳሰበው፡፡
ህብረተሰቡ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረግ ቢሮው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን የድንገተኛና የመስክ ክትትል፥ ምልከታና የሰዓት ቁጥጥር ተግባሩን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንደሚያከናውንም ገልጿል፡፡