የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ከመንግሥት የተሰጠውን መመሪያና ደንብ ችላ በማለት ከሕግ ውጪ ነዳጅ የጫኑ ስምንት የነዳጅ ቦቴዎች መውረሱን አስታወቀ፡፡
ሆን ብለው የነዳጅ እጥረት እንዲከሰትና ከመንግሥት የተሰጠውን መመሪያና ደንብ ችላ በማለት ከሕግ ውጪ ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ወደ ከተማ እንዳይገቡ ያደረጉ ስምንት የነዳጅ ካምፓኒዎች ቦቴዎች በዛሬው እለት በፀጥታ ኃይሎችና በኅብረተሰቡ ጥቆማ ተወርሰዋል፡፡
የተወረሰው ነዳጅም በነዳጅ ማደያዎች በኩል እንዲከፋፈል ማድረጉን ቢሮው አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ መስፍን አሰፋ ሕግ አክብረው በማይሰሩና በትክክል ስራቸውን በማይወጡ የነዳጅ ካምፓኒዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡