ታላቁን የረመዳን ጾምና መጪውን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ ቢያፍ ማንፋክቸሪን የግል ድርጅት ለማዕድ ማጋራት የሚሆን ድጋፍ 200 ኩንታል ስንዴና 400 መቶ ጀሪካን ባለአምስት ሊትር ዘይት ድጋፍ ለሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች በከተማ አስተዳደሩ በኩል ተደራሽ እንዲደረግ ለከንቲባ ጽ/ቤት አስረክበዋል ።
ድጋፉን የቢያፍ ማንፋክቸሪንግ ድርጅት ባለቤት አቶ ደረጀ በድሉ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስረክበዋል ።
የቢያፍ ማንፋክቸሪንግ ድርጅት በአይነት ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ያስረከበው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር መሆኑን የጠቀሱት የድርጅቱ ባለቤት አቶ ደረጄ ፤መንግሥት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመርዳት ከሚያደርገው ጥረት ባሻገር ሁላችንም ከሞላልን ላይ ሳይሆን ካለን ቀንሰን በመደገፍ ማሕበራዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ በበኩላቸው ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ረገድ ድጋፍ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን እንደ ቢያፍ ማንፋክቸሪንግ ያሉ ማሕበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ድርጅቶችና ግለሰቦች ድጋፍ ፤በሚፈለገው ልክና መጠን የወገን እርዳታ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ማድረግ እንዲቻለን አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ለአስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ቢያፍ ማንፋክቸሪንግ ያስረከበው የአይነት ድጋፍ በአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር በኩል፤ በክፍለ ከተማው የሚኖሩ ድጋፍ ለሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጥ መሆኑ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ተገልጿል።