የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል::
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የማጠቃለያ ንግግር እና የስራ አቅጣጫ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ብልሹ አሰራርና ሌብነትን የመከላከል ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል::
አገልግሎት አሰጣጥን ከወቅቱ ጋር እንዲሄድ ለማስቻል በርካታ ዘርፎችን የማዘመን እና የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል::
የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ጫናን በመቀነስ የነዋሪውን ችግር እንዲያቀሉ የተጀመሩት የእሁድ ገበያ እና የሌማት ትሩፋት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለፁት ከንቲባ አዳነች በተለይም በእሁድ ገበያ መሰረታዊ ፍጆታ የሆኑ ምርቶች በቀላሉ ህብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል::
አስተዳደሩ ከተማዋን ለነዋሪዎችዋ ጽዱ ውብና ምቹ ከማድረግ ባሻገር ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ከተማነትዋን የምትመጥን ለማድረግ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ተግባራዊ እያደረገ ነውም ብለዋል::
ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር አመራራችን ፅንፈኝነትን, ጥላቻን, የህብረተሰቡን አንድነት የሚንዱ አስተሳሰቦችን, የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረጉ የሚዲያ ዘመቻዎችን እንዲሁም ሌሎች የፓርቲያችን እሳቤ ያልሆኑ አመለካከቶችን በመዋጋት ረገድ እየሰራ ያለው ስራ ብዙ ቢሆንም አሁንም ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት እና በህቡእ አደረጃጀት የሚደረግ ህገወጥነት ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል::
በቀሪ የበጀት አመቱ ወራት ያልተከናወኑ ተግባራት ተለይተው በእቅድ ክለሳ እንዲካተቱ በማድረግ የህዝባችንን ኑሮ የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩም ከንቲባ አዳነች አክለው ገልጸዋል::