የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ በጋር በመሆን በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ ዳያስፖራ ባለሀብቶችን የሚያበረታታ እና ግንዛቤ መፍጠሪያ ፎረም በስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዷል።
ሀገራችን ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሏት የተናገሩት ፥ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በሁሉም አካባቢዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመጠቀም ሃገራቸውን እና አዲስ አበባን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ አካላት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በጤና፣ ግብርና፣ በትራንስፖርት ሎጀስቲክ፣የማምረቻው ዘርፍ፣ የቱሪዝም ልማት፣ የሃይል ዘርፍ እና የማዕድን ዘርፎች ለዲያስፖራ ባለሃብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሆናቸውን ም/ከንቲባው አስረድተዋል፡፡
በኢንቨስትመንት መሰማራት እና በዕድሉ መጠቀም ለሚፈልጉ ባለሃብቶች investethio.com የሚለውን የኮሚሽኑን ድረ ገጽ መመልከት እንደሚችሉም ተጠቁሟል።
የኢ.ፊ.ዴ.ሪ ኢንቨስትመንት ኮሚሸን ኮሚሽነር ወ/ሮ ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ሀገራችን በብዙ ችግር ውስጥ ሁናም ባለፋት አምስት ወራት የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት መሳብ አንደተቻለ ተናግረዋል።
የዲያስፖራው ማህበረሰብ መዋል ንዋያቸውን በሀገራቸው እንዲያፈሱ እና ወደ መጡበት ሀገራት ሲመለሱም ለሌሎች ባለሀብቶች በሀገራችን ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማሳወቅ የአምባሳደርነት ሚናቸውን እንዲወጡም ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ጠይቀዋል።
በፎረሙ ከአምስት በላይ የሚሆኑ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ያሏቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮች አቅርበዋል።