“አዲስ ፖለቲካዊ ዕይታ – አዲስ ሀገራዊ እምርታ!” በሚል ለክፍለ ከተማ እና ለወረዳ አጠቃላይ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቀቀ።
በስልጠናው ማጠቃለያ የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የማጠቃለያ ሀሳብ እና የቀጣይ የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የብልፅግና አመራር ሰላምን በማንገብ ሀገራዊ ብልፅግና እውን እንዲሆን በማድረግ ረገድ ያለው ሚና እና አስተዋጽኦ ከፍ ያለ በመሆኑ አመራሩ በታማኝነትና በቅንነት ስራዎችን መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።
ብልፅግና ብዝሃነትን የተቀበለ፣ ብዝሃነትን የሚያከብርና በአግባቡ እውቅና ሰጥቶ የሚንከባከብ ነው ያሉት ከንቲባዋ ሀገራዊ አንድነታችንን ደግሞ የሚያጠናክር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የፓርቲ አደረጃጀቶች ውጤታማ ተግባር እንዲሰሩ ከማድረግ አንፃር መደገፍና ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ የተናገሩት ከንቲባ አዳነች በአላማ በመጽናት፣ በጋራ በመቆም፣ ተጠያቂነትን በማስፈንና በአገልግሎት ዘርፉ ውጤታማ ተግባራትን በመከወን ለህዝቡ በምርጫ ወቅት የገባነውን ቃል መፈጸም እንደሚገባ አንስተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው ለአመራሩ የተሰጠው ስልጠና የአመለካከት ክፍተቶችን የሞላ፣ ትውልድን ታሳቢ ያደረገ እና የአመራሩን ችግሮች በመለየት የመፍታት አቅምን ያዳበረ እንደነበረ ገልጸዋል።
አመራሩ በቀሪ የተግባር ምዕራፎች የተቋም ግንባታን በማጠናከር ያሉትን ስራዎች በጥራትና በውጤት መተግበርና መፈጸም እንደሚገባውም አቶ መለሰ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ላሉ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች በሁለት ዙር የተሰጠው ስልጠና በቀጣይ ቀናትም እስከ ታችኛው አመራር እና አባል ድረስ የሚሰጥ መሆኑ በማጠቃለያ መድረኩ ተገልጿል።