ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ በተገኙበት ከከተማዋ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ለመከላከያ ሠራዊት በሚደረገው ድጋፍ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል ።
ኢትዮጵያውያን ደስታችን ሙሉ የሚሆነው ሁሉም እጅ ለእጅ መያያዝ ሲኖረን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እኛ ስንተባበር እና ስንተጋገዝ የማናሳካው ጉዳይ እንደሌለ የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣የ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እና ሌሎች ተግባራት ጉልህ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ወጣቶች በጁንታው ርዥራዦች የሚነዛውን የውሸት የማህበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ወደ ጎን በመተው ለጀግናዉ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በሚችሉት አቅም ማገዝና ደጀንነታቸዉን ማረጋገጥ እንደሚገባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጥሪ አቅርበዋል ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተና ጄነራል ባጫ ደበሌ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን ለማሳየት በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ በማጠናከር ረገድ እያደረገ ያለው ተግባር ለሠራዊቱ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ መሆኑን ገልጸዋል ።
የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ ያለ አንዳች ሁከት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምስጋና አቅርበዋል ።
በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች በበኩላቸው የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ለማስጠበቅ ሌት ተቀን በመጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል ።
የመከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተና ጄነራል ባጫ ደበሌ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከወጣቶች ስጦታ ተበርክቶላቸዋል ።