አራዳ ክፍለ ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹና ማራኪ ለማድረግ “አራዳን እንደገና” በሚል በዘጠና ቀን የተሰሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ጨምሮ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ የህዝብ ወኪሎችና የልማቱ ተጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ነዋሪዎች በተገኙበት ተመርቋል።
የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በፕሮጀክቶቹ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ለማድረግ በለውጡ መንግስት በቤተ መንግስት የተጀመሩት የልማት ስራዎች በከተማችን በ 90 ቀናት ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስገንዝበዋል።
በ 90 ቀን የልማት ፕሮጀክቶች የአመራሩም፣ የህዝባችንም የልማት ተነሳሽነት እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ሞገስ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎችና ባለሀብቶ ተሳትፏቸውን በማጠናከር የአራዳን ስምና ታሪኳን የሚመጥኑ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማስፋት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ያሉንን አቅሞች ካስተባበርን ለልማት ካዋልን ከተማችንም ብሎም ሀገራችንን መለወጥ እንችላለን ያሉት አቶ ሞገስ በቀጣይም በሚኖሩን ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ቀን ከሌሊት እየሰራን ለህዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር እያረጋገጥን እንቀጥላለን ብለዋል።
የአራዳ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሞላ ንጉስ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት ወራት በከተማ አመራሩ የቅርብ ድጋፍና ክትትል፣ በባለሀብቶችና በነዋሪዎች ተሳትፎ ከ 342 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የነዋሪውን ህይወት የሚቀይሩና የክ/ከተማውን ገፅታ ያሻሻሉ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ከ90 ቀናት የልማት ስራዎች መካከል ክፍለ ከተማውን ውብና ማራኪ ለማድረግ በተሰሩት ተግባራት በርካታ ብሎኮችንና ትምህርት ቤቶችን በፅዳት ሞዴል የማድረግ ስራ መከናወኑን መቻሉን እና የቤት ችግርን ለማቃለልም ባለ ስድስት ወለልና ባለ ሶስት ወለል ህንፃዎች በባለሀብቶች እየተገነቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የመንገድ ዳር አካፋዮች፣ አደባባዮች፣ 70 እና 100 ደረጃን ማስዋብ፣ የወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የዳቦ ፋብሪካና መሸጫዎች እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚረዳ ዲጂታል የሰአት መቆጣጠሪያ ባለፉት ዘጠና ቀናት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል። በሌማት ቱሩፋት እና በከተማ ግብርና ስራዎችም ከስደት ተመላሾችና የክ/ከተማው ነዋሪ ተጠቃሚ እንዲሆን አበረታች ጥረቶች መደረጋቸው ተጠቁሟል።
በፕሮግራሙ ላይ በአራዳ ክ/ከተማ ባለፉት 90 ቀናት በተሰሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ላይ የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች የእውቅና እና የምስጋና ስጦታ ተበርክቷል።