በአዲስ አበባ 4 ኪሎ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው አብርሆት ሁለገብ ዘመናዊ ቤተ መፃሕፍት አሁን ተመርቋል።
ቤተመፃሕፍቱን የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ ፤ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መርቀውታል።
በ19 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው እና ዛሬ የተመረቀው ዘመናዊ ቤተመፃሕፍት በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ 10 ቤተ-መፃሕፍት መካከል መሆኑ ተነግሮለታል።
ቤተመፃሕፍቱ በ4 ወለሎቹ 1.4 ሚሊዮን መፃሕፍትን መያዝ የሚችል 1.5 ኪ.ሜ መደርደሪያ እንዳለው ተገልጿል።
ቤተመፃሕፍቱ ከ240 ሺህ በላይ መፃሕፍትና 300 ሺህ ጥናታዊ ፅሁፎችን የያዘ መሆኑም ተመልክቷል።
የህፃናት ማንበቢያ እንዲሁም ማየት ለተሳናቸው አንባቢዎች በቂ የብሬይል መፃሕፍት አቅርቦት ያለው መሆኑም ልዩ ያደርገዋል።
ዘመናዊ ካፍቴሪያና የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ስምንት የመፃሕፍት መሸጫ ሱቆች፣ አምፊ ቲያትርና መጫወቻ ቦታዎችንም ያካተተ ነው።
በተጨማሪም ደህንነቱ የተጠበቀ በአንዴ 115 መኪኖችን ማስተናገድ የሚችል የመኪና ማቆሚያ የያዘ ነው።