አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ከኅዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሌሊት 6 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለጸ።
የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየሁ ማሞ፣ “ቤተ መጻሕፍቱ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ታሪክ ሠሪ ትውልድ በንባብ የሚገነባበት ማዕከል ነው” ብለዋል።
በንግግር እና ውይይት የሚያምን ትውልድ የሚገነባው አንባቢ ትውልድ ሲፈጠር መሆኑን ጠቅሰው፣ የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አንባቢ ትውልድን ለማፍራት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
ቤተ መጻሕፍቱ ከዚህ ቀደም ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ብቻ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር አውስተው፣ ተጠቃሚዎች የአገልግሎት ሰዓት እንዲራዘም ሲጠይቁ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት አገልግሎት የሚሰጥበት ሰዓት ማሻሻያ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከኅዳር 14 ጀምሮ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት ድረስ ቤተ መጻሕፍቱ ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ማሳወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።