የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ምክትል ከንቲባ እና የሥራ፣ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ተወካዮች ጋር የኢንዱስትሪ ልማትን ማሳደግ በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ዉይይት አድርገዋል፡፡
በዉይይቱ አቶ ጃንጥራር እንደተናገሩት ከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪ ልማትን ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለዉ ተናግረዉ ኢንደስትሪዉን ለማሳደግ የሚያግዝ አላማ ይዞ ለሚመጣ ማንኛዉም አለም አቀፍ ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑና አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ክቡር አቶ ጃንጥራር አክለዉም አለማቀፍ ድርጅቶች ወደ ሀገር ሲገቡ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ እቅድ መያዝ አለባቸዉ ብለዉ በከተማችን የመስሪያ ቦታ ፍላጎት እና አቅርቦት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ለስራ ምቹ የሆኑ መስሪያ ቦታ ግንባታ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በመጋበዝ ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(UNIDO) ተወካይ በበኩላቸዉ ድርጅቱ በዋናነት በአቅም ግንባት፣በቆዳና የቆዳ ዉጤቶች፣በጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም ማህበራዊ ግዴታዎችን መወጣት ላይ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልፀዉ ቢሮዉም ከነሱ ጋር ለመስራት ያሳየዉ ተነሳሽነትን አድንቀዋል፡፡